አባይ ሚዲያ ዜና-ጥቅምት 28፣2012

ከሰሞኑ የአማራን ህዝብ ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም  አዴፓ፣ አብን፣ አዴኃን፣ መአህድ፣ መላው አማራ ህዝብ ፓርቲና ነፀብራቅ አማራ በሚያስሟሟቸው አጀንዳዎች ላይ አብረው ለመስራት የተስማሙት ፓርቲዎች መሆናቸው ይታወሳል።

ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ርዕዮተ ዓለም ከመከተላቸው አንፃር እንዲሁም የአማራን ህዝብ ጥቅም አልወከሉም በሚል ከመወነጃጀላቸው ጋር ተያይዞ በምን አይነት ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት ስምምነት ላይ ደረሱ የሚለው ጥያቄን የሚያስነሳ ነው።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለተመሳሳይ ህዝብ እንደመስራታቸው መጠን ምንም እንኳን ፕሮግራማቸውም ሆነ ሌሎች የሚለያዩዋቸው ጉዳዮች ቢኖርም አብሮ ለመስራቱም መሰረቱ እንወክለዋለን የሚሉት ህዝብ ልማትና ብልፅግና እንደሆነ የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይናገራሉ።

ዶ/ር ደሳለኝ “ከመጠላለፍ ወጥተን ወደ መተባበሩ እንድናተኩር፤ የምናደርጋቸውም ውድድሮች በሰለጠነና በሰከነ መንገድ እንዲሆን ስምምነት ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

የአዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተተካ በቀለ በበኩላቸው “መድረኩ የሚለየው ከመጠላለፍ ወጥቶ በሰከነ ፖለቲካዊ ትግል ውስጥ ለማለፍ መንገድ የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

በፖለቲካው ዘርፍ ስምምነት ላይ ከደረሱባቸው መካከል የተወሰኑትን ዶ/ር ደሳለኝ  እንደጠቀሱት ፓርቲዎቹ በማንኛውም እንቅሴያቸው ላይ ስም ከማጠልሸት፣ ከመወነጃጀልና ከመጠላለፍ መታቀብ፤ ወጣቱን በጋራ አቅጣጫ ማስያዝ፤ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አብሮ መስራት ናቸው።

“ለዘመናት የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጠላለፍና የመገዳደል ባህልንም የሚያስቀር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ይህ ነው የሚባል ልዩነት የለንም” በማለትም አቶ ተተካ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ዶ/ር ደሳለኝ ህወሓትና አዴፓ ከአስርት ዓመታት በላይ በእህትማማችነት በኢህአዴግ ውስጥ ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም በቅርብ ጊዜያት ግን በግልፅ ተቃርኗቸው እየታየ ነው ሲሉ አክለዋል።