አባይ ሚዲያ ዜና-ጥቅምት 28፣2012

ለአምስት ቀናት የሚቆየው የግንባሩ አራተኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ትላንት በጎዴ ከተማ  መካሄድ ጀምሯል።

የግንባሩ ሊቀመንበር  አድሚራል መሐመድ ዑመር ጉባዔውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ከነጻ አውጪነት ወደ ፓርቲነት ራሱን በመቀየር ለመንቀሳቀስ ይፈልጋል ያሉ ሲሆን ለዚህም ጉባዔው የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚነድፍበት እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

ድርጅቱ በአገራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የግንባሩ የአባላት ጉዳይ ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢብራሂም በበኩላቸው ግንባሩን በፓርቲነት የሚንቀሳቀስበትን ስትራቴጂ ለጉባዔተኞች ለውይይት በማቅረብ የሚያጸድቅ ሲሆን በተጨማሪም ለ21 ዓመታት ባገለገሉት የግንባሩ ሊቀመንበር ምትክ ምርጫ ያካሄዳል።

ለዚህም በማዕከላዊ ኮሚቴው በዕጩነት ካቀረባቸው አቶ አብዲራህማን ሼህ መህዴ (መዳይ) ና አቶ አህመድ ያሲን አንዳቸው ጉባዔተኞቹ ይመርጣሉ።

በጉባዔው ከ700 በላይ የግንባሩ አመራርና አባላት፣ ደጋፊዎች፣የክልሉ ገዢና የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢዜማና የአብን ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በኦብነግ 4ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ በመገኘት የአጋርነት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአብን ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) አብን የኢትዮጵያ አገረ መንግስት ጉዳይ አንዴ ተሰርቶ የሚጠናቀቅና ተገንብቶ ያለቀ ጉዳይ ነው ብሎ አያምንም ያሉ ሲሆን አማራው፣ ኦሮሞው፣ ሶማሊው፣ ትግሬው ሁሉም በወርዱና በቁመናው ልክ የሚወከልበት፤ ድምፁ እኩል የሚሰማበት፣ የመላው ኢትዮጵያዊያን መብት የሚከበርበትና ግዴታቸውን የሚወጡበት አገር ማድረግ እንችላለን ሲሉ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገኝተው የኦብነግ አባላት ለሕዝባቸው መብት መከበር ሲሉ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር መራር ትግል እንዳደረጉ እና ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈሉ አስታውሰዋል።

በቀጣይም የዜጎችን ጥያቄ ለመመለስ ሁለቱ ድርጅቶች ያነገቡት የማኅበራዊ ፍትህ የፖለቲካ ፍልስፍና በመሆኑ አብረን እንሠራለን ሲሉ የፓርቲያቸውን ፍላጎት ሊቀመንበሩ አሳውቀዋል።