አባይ ሚዲያ ዜና-ጥቅምት 28፣2012

የትግራይ ተወላጆች በአማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይሄዱ ጥሪ አቅርቦ የነበረው የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የተላለፈው መልዕክት እኔን አይወክለኝም ሲል አስተባበለ፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች መግቢያ ጊዜ መቃረብን ተከትሎ ከሳምንታት በፊት የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ በአማራ ክልል የደኅንት ስጋት ስላለ በሚል ተማሪዎች ወደ ክልሉ እንዳይሔዱ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

አባይ ሚዲያ በወቅቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የክልሉ ትምህርት ቢሮ መልዕክት ተገቢ አይደለም ስለማለቱ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን ተማሪዎችን የመመደቡ ሥራ የሚንስቴሩ ብቻ እንደሆነና ተማሪዎች በተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገኙም መምክሩ አይዘነጋም፡፡

በርካታ የትግራይ ክልል ተወላጆች ወደ ተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ቢገቡም ጥቂት የማይባሉት ግን የቢሮውን ምክር ተቀብለው ወደ አማራ ክልል አለመሔዳቸውን የመረጃ ምንጮቻችን አመልክተዋል፡፡

የቀሩት ተማሪዎችም ከሰሞኑ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ‹እንድንቀር ሲመክረን በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትማራላችሁ በሚል ነበር በማለት አሁን ላይ ቃሉ የውኃ ሽታ ሆኖብናል› ሲሉ እያማረሩ መሆኑን የአማራ ብዙሃን መገናኛ ዘግቦ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ አሐዱ ቴሌቪዥን ጠይቄዋለሁ የሚለው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ‹‹ቀድሞውኑ የትግራይ ተወላጆች በአማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይሄዱ ጥሪ አላቀረብኩም፣ የተላለፈው መልዕክትም ቢሮውን አይወክልም›› ሲል መልሷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ‹‹እኛ አትሂዱ ማለት አንችልም ተማሪዎችን የመመደብ ስልጣን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ነው ተማሪዎች ሄደው መማር ይችላሉ ከዚህ በፊት የወጣው መግለጫ ከኛ አይደለም›› ሲሉ ነው ያስተባበሉት፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ‹‹አብዛኞቹ ተማሪዎቻችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ገብተዋል ከወሬ የዘለለ ነገር የለም›› ሲል ተናግሯል፡፡