አባይ ሚዲያ ዜና-ጥቅምት 28፣2012

በጀርመን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ኮሚቴ ራሳቸውን “ቄሮ” በሚል ስም አደራጅተው በጀርመን የተለያዩ ከተሞች ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ ጉዳይ ለመምከር የጠሩትን ስብሰባ በኃይል በማወክ ወንጀል ፈፅመዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ በፍራንክፈርት ከተማ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱን አስታውቋል ሲል ዶይቼ ቨለ ዘግቧል ።

የኮሚቴው ዋና ሊቀመንበር አቶ ስዩም ኃብተማርያም ለዶይቼ ቨለ እንዳስረዱት ግለሰቦቹ በስብሰባው አዘጋጆች እና በዕለቱ የክብር እንግዳ ላይ የኃይል ጥቃት እንደሚፈፅሙ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በቪድዮ ጭምር መልዕክቶችን ከማስተላለፋቸውም ሌላ ዘር እና ሃይማኖት ተኮር ስድቦችን በመሳደብ ተሰብሳቢዎችን በማሸማቀቅ እንዲሁም ፎቶግራፍ እና ቪድዮ እያነሱ በማስፈራራት ከፍተኛ የመብት ጥሰት እና ሽብር ፈፅመዋል ሲሉ ከሰዋል።

አዘጋጆቹ ያለ ብሄር እና ሃይማኖት አድልዖ አስገብተን እንዲወያዩ አድርገናል ያሉ ቢሆንም በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት ወገኖች ስብሰባው “ለኢትዮጵያውያን በሙሉ” ተብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም ኦሮሞ እና ሙስሊሞች ተለይተው ወደ ውስጥ እንዳይገቡ አድሎ ተፈፅሞብናል ብለዋል:: የግለሰቦቹ ተወካይ የሆኑት አቶ አብዲ አባጀበል ጥቂቶች የገባነው የምናውቃቸው ሰዎች “እነሱ አይረብሹም” ብለው ስለመሰከሩልን ያሉ ሲሆን የቄሮ ወጣቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በህብረተሰቡ ላይ ምንም ዓይነት የመብት ጥሰት አይፈፅሙም፡፡

በጀርመን የሽብር ጥቃቶች ሳይንሳዊ ተንታኝ ባለሙያና የኮሚቴው የህግ ጠበቃ ስቴፈን ኩን ተጠርጣሪዎቹ በጀርመን ሕገ መንግሥት ትኩረት ተሰቶት በመጀመሪያ ምዕራፍ የሰፈረውን የሰዎችን በነጻነት ሃሳብን የመግለፅ እና የመሰብሰብ መብት በሃይል በማፈን የክስ ፋይል ከፍተናል።”ሲሉ ገልፀዋል።

በወቅቱ ለተፈፀመው ችግርም በቂ የምስክር መረጃ ስላለን በሃሰት ክስ ከተመሰረተብን በህግ እንከራከራለን ሲሉ አቶ አብዲ አባጀበል መልስ ሰተዋል።

ተከሳሾቹ የክስ መጥሪያ እንደደረሳቸው የፍርድ ሂደቱ በፍራንክፈርት ፍርድቤት እንደሚጀመር የኮሚቴው ዋና ሊቀመንበር አቶ ስዩም  አስረድተዋል።