አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 15፣2012

ከአሁን በፊት በድሬዳዋ ከተማ በተነሱ ግጭቶች ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣትና ህግን ለማስከበር የከተማዋ ፖሊስ ቸልተኛ እንደነበርና ወገንተኝነት አሳይቷል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

በዛሬው ዕለትም ይህንን ሀሳብ የሚያስተባብል መግለጫ አውጥቷል፡፡

ኮሚሽኑ በድሬደዋ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝ ደረጃ በማስፈንና በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን እዉን ለማድረግ የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን ተቋማዊና ሞያዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት በተግባር ስራዎችን እያከናወነ በለዉጥ ሂደቱ ወስጥ የሚገኝ ተቋም ነዉ ብሏል።

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኮሚሽኑን መግለጫ በመኮነን ከአመት በፊት ድሬዳዋ ላይ የነበሩ አንድ ከፍተኛ አመራር ከተነሱ ወዲህ ፖሊስ ስራውን በአግባቡ እየሰራ እንዳልሆነና ህግ የማስከበር አቅሙ ዝቅተኛ እንደሆነ ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት በአንጻራዊ መረጋጋት ውስጥ ብትገኝም መከላከያ የከተማዋን አካባቢዎች ተቆጣጥሯል፡፡

የድሬዳዋ ፖሊስ የዘረኝነት መንፈስ እያሳየ እንደሚገኝ የገለጹት ነዋሪዎቹ ህግና ስርዓት ሲጣስ ምንም አይነት መከላከል ያላደረገው ፖሊስ ዛሬ ላይ ማስተባበያ ሊሰጥ እንደማይገባውም ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

በድሬዳዋ ለሳምንታት በዘለቀ የጥፋት ሀይሎች እንቅስቃሴ ዘርና ብሄርን ትኩረት ያደረገ ጥቃት ሲፈጸም እንደነበር ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡