መሪዎቻችን ለምን እልከኛ ይሆናሉ ዶ/ር አብይስ  እንደዚያው ይሆኑ ይሆን ወጣቶችስ ሙህራኑስ አላሳፈሩንም ወይ( ከተስፋሁን አረጋይ) 

በሀገራችን ሰላማዊ ለዉጥ የሚደረግባቸው በጣም ብዙ እድሎች በመሪዎች ግትርነት እና እራስ ውዳድነት ምክንያት ሲሰናከሉ ኖረዋል፤ በአጼ ሃ/ስላሴ ዘመን የመሬት ላራሹ ጥያቄና የህገመንግስት ማሻሻልን ጉዳይ አጼዉ ቢቀበሉ ኖሮ ቦኋላ የመጣው እልቂት ኣይከተልም ነበር።   ንጉሱ  ስለ ታላቁዋ ብርታንያ እና ሌሎችም አገሮች ኮንስቲትውሽናል ሞናርኪ ያውቁ ነበር።  ያን እይነት ኣስተዳደር በሃገራቸው እንዲመሰረት ፈቃደኛ ቢሆኑ ኖሮ የደረሰብን ችግር በሙሉ በዚያ መልክ ባልመጣ ነበር፤ የራሳቸው ቤተሰቦችም ይህን አይነት ድቀት ባልደረሰባቸው።  ከዚያ ቀጥሎ የገዛን የመንግስቱ ሃይለማሪያም መንግስት (ደርግ) የሚቀርቡለትን ምክሮችና የማሻሻያ ሀሳቦችን ቢቀበል ኖሮ ቦኋላ የተከተለው ውርደት ባልደረሰበት፤ ደርጎች እንኳንስ የውጭ ሃይሎችን ምክር ለመስማት ቀርቶ በውስጥ የነበሩትን የነ ጀኔራል አማንን የነ ሲሳይ ሃብቴን የነ አጥናፉ አባተን እና የመሳሰሉትን የደርግ መሪዎች ሃሳብ የሚሰማ ጆሮ ኣልነበራቸውም። ደርግ ኢሕአፓን “የጊዚያዊ ህዝባዊ መንግስት” ጥያቄ በማቅረቡ ከጨፈጨፈ ቦኋላ በዙሪያው የነበሩትን መኢሶንን፤ኢጭአትን፤ወዝሊግን እና ማሊሬድን ውሃ ቀጠነ እያለ ተራበተራ ሲያጠፋቸው በዙሪያው የነበሩት ሙህራን ሁሉ በርግገው በአስር አለቃ ካድሬዎች ብቻ የተሞላው ሰደድ የሚባለው ቡድን ሲቀር ወደ ኢሠፓነት ተለወጠ። ደርጎች በጊዘው ጎልቶ የወጣው እና በህብረተሰቡ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረውን የ”ጊዜኣዊ ህዝባዊ መንግስ” ጥያቄ በማጥላላት ሃሳቡን የሚደግፉትን ሃይሎች በሙሉ በመጨፍጨፍ ጆሮኣቸውን ዘግተው በድንቁርናቸው ቀጠሉ፤ ይህ የጊዚያዊ ህዝብዊ መንግስት ጥያቄ እራሱን ደርግን ጭምር የሚያሳትፍ ለውጡን በሰላማዊ መንገድ የሚያስኬድ የመፍትሄ ሃሳብ ሆኖ ሳለ ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆነው ግትሩ ደርግ ህብረ ብሄር ሃይሎችን በመጨፍጨፍ ለጠባብ ብሄርተኛ ሃይሎች ሁኔታዎችን አመቻችተው በመጨረሻም እራሳቸውን አዋርርደው አገሪቱን ለከፍተኛ አደጋ ካጋለጡ ቦኋላ ደርጎች ተሰልፈው ለሚንቁዋቸው ወያኔዎች እጃቸውን በመስጠት በገነቡት እስር ቤት ተሰባሰቡ።  

በአቶ መለስ የተመራው ወያኔ/ኢህአዴግ ደግሞ ለ27 ዓመት ሙሉ በእብሪት እና በእልህ ከህዝብ እና ከድርጅቶች የሚቀርብለትን የእርቅ፤ የሰላም እና የአንድነት አጀንዳዎች በንቀት ሲሳለቅባቸው ኖረ። የህግ እና የፍትህ ጥያቄ ሲዋረድ አየን፤ ሰብዓዊይ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተንቀው ህዝብ እንደጉድ ተዋረደ፤ እስር ቤቶች በወጣቶች ተሞሉ ከዚህም አልፎ ሰዎች እየተገደሉ በየኩሬው ተቀበሩ፤ ይህም በአንዳንድ አካባቢ የሃገር ሉዓላዊነት እና ሃገራዊ ፍቅር ቦታ አጥተው ሃገራዊ ስሜቱ በጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አደረገ፤ ወያኔ/ኢህአዴግም እንደ ደርግ በግድያም ባይሆን በውስጡ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሃይሎች እየነቀለ ማውጣቱን  ያውቅበት ነበር፤ እንኳን ሌላው ቀርቶ በወያኔ ውስጥ ይከበሩ የነበሩትን እነ አረጋዊ በርሄን ነቅሎ ለባረር ከፍተኛ ትብብር ሲያደርጉ የነበሩትን እነ እሰየ አብርሃን እንደቀልድ አባሯል እነ ታምራት ላይኔን እንደ አሻንጉሊት መሳቂያ አድርጓቸዋል። በአቶ መለስ የተመራው ወያኔ/ኢህአዴግ የህዝብን መብት የሃገርን ሉዓላዊነት ሲያዋርድ ቆይቶ አቶ መለስ ቢሞትም እንኳ ለመለስ መንፈስ የሚገዙ መሪዎች በመተካታቸው ህዝባዊ ትግሉ በከፍተኛ ደረጃ ተቀጣጥሎ በመምጣቱ የነአቶ  ለማን ቡድን ወለደ፤ የጎንደርን ሱናሜ የአምቦን ነጎድጓድ ግምት ውስጥ በማስገባት የህዝብ ወገን እንሆናለን ብሎ የመጣው የለውጥ ሃይል የሃገራችን ችግር በመገንዘብ ሃገራዊ መፍትሄ ለማምጣት ዝግጁ ነኝ ብሎ ሲነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ቂም በቀሉን ትቶ ለለውጡ ሃይል ይሄ ነው የማይባል ድግፍ ሰጠ፤  በህዝቡ እና በትግል ላይ በነበሩት ሃይሎች በሰፊው ትግል ሲደረገባቸው የቆዩትን ጥያቄዎች በተለይም፦

        _የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ

        _የሽግግር መንግስት ጥያቄ

        _የሃቀኛ ፌዴራሊዝም ጥያቄ

        _የህገመንግስት ጥያቄ

        _የዴሞክራሲ ጥያቄ

        _የሃገር ሉዓላዊነት ጥያቄ  ወዘተ ወዘተ

በአግባቡ ሳይመለሱ “ግድ የለም እኛን እመኑን  ሁሉንም ጥያቄ በስነስርዓት እንመልሳለን፤ እመኑን በሰራነው ስህተት ተጸጽተናል ይሄን በማረም እናሸጋግራችኋለን” እያሉ አብረውን በማልቀስ በትህትና ህብረተሰቡን ለማግባባት በመሞከራቸው ህዝቡም ሆነ በትግል ላይ የቆዩት ሃይሎች ሲታገሉላቸው የቆዩላቸውን  ጥያቄዎች ሁሉ ለዘብ አድርገው ለለውጡ ሃይል እድል ለመስጠት ሞከሩ። ታዲያ ምን ያደርጋል ባለመታደል በተጠበቀው መልክ የለውጡ ሃይሎች ላሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ለመስጠት አቅም ሊገነቡ አልቻሉም፤ እንዲያውም ከቀን ወደ ቀን እየተደናበሩ መጡ፤ ለውጡን ለመምራት የሚጠቀሙት ያን የበሰበሰ የኢህአዴግ ቡድን በመሆኑ ኢህአዴጎቹ ያደጉበትን ክልልተኛ ፖለቲካ ትተው ዴሞክራሲያዊይ እና ሃገራዊ ክብርን እንዲቀበሉ አላደረጋቸውም፤  እንዲያውም አጋጣሚውን በመጠቀም በማናለብኝነት በየክልላቸው የቡድን ፍላጎታቸውን የሚያስፈጽም ታጣቂዎችን በማደራጀት ማእከላዊዩን መንግስት ከመፈታተን አልፈው በሃገራዊ ሉዓላዊነታችን ላይ አደጋ እየሆኑ መጥተዋል፤ ማእከላዊዩም መንግስት እነዚህን ታጣቂ ሃይሎች ተገን አድርገው  የሚፈጠሩትን ስርዓት አልባ እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር ቢሯራጥም በድርጅት መስመራቸው የቀደዱት ሰፊ ክፍተቶች በመኖሩ ችግሩን  ለመፍታት ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መጥቷል። ይህ በሚሆንበት ወቅት ለውጡን የሚመራው ሃይል የተፈጠሩትን ችግሮች ሁሉ በመገምገም ከሌላው አቅጣጫ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ናቸው በሚል ህሳቤ ከዚህ በፊት የቀረቡላቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች (ለምሳሌ ብሄራዊ እርቅ፤ የሽግግሩ መርሃ ግብር ወዘተ) ወደ ህብረተሰቡ በማቅረብ እነዚህን የመፍትሄ ሃሳቦች ከመፈተሽ ይልቅ አሁንም እንደ ድሮዎቹ መሪዎቻችን በእልህ የኛን መንገድ ብቻ ተከተሉ የሚለው የለውጡ ሃይል አካሄድ አግኝተውት የነበረውን ድጋፍ እየሸረሸረው ከመሄዱም በላይ ሃገሪቱን ከከፍተኛ አደጋ ላይ እየጣላት ነው። ይገባኛል በኢህአዴግ  ውስጥ ያለው ሃይል የብቃት እና ያስተዳደግ ችግር አለበት፤ በውስጣቸው ያለው ሽኩቻም ይህን ሃገራዊ ሃላፊነት እንዲወጡ አያደርጋቸውም፤ ግን ኢትዮጵያ ማህጸነ ሰፍ ነች፤ ይህን ዓላማ ስልጣን ሳይፈልጉ ከስልጣን ላይም ሳይቀመጡ በህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ እና ህዝባቸውን በማቀራረብ በሃገሪቱም ሰላም ለማስፈን የሚችሉ ብዙ  ልጆች ስላልዋት ምነው እነ ዶ/ር አብይ እድሉን ቢያመቻቹላቸው። የአጼው፤ የመንግስቱ እና የነመለስ ግትር የእልከኝነት መንገድ እነሱን አዋርዶ ሃገሪቱን ለምን ዓይነት ችግር እንዳጋለጣት ከታሪክ ተምራችኋል። እናንተስ እራሳችሁን ከውርደት ሃገሪቱን ከጥፋት የምታወጡበትን መንገድ ከሃገሪቱ ሙህራን እና አገር ወዳድ ዜጎች ጋር በመመካከር የሌላውንም ሃሳብ በቅንነት በመቀበል በመተማመን እንድትሰሩ እግዚአብሄር ይርዳን ትላላችሁ ወይ፤ ይህን እድል በአግባቡ ከተጠቀማችሁበት ህዝብ ከጅምሩ የቸራችሁን ፍቅር እና ክብር እንደገና ያጎናጽፋችኋል፤ እንደ ቴዎድሮስ እንደሚኒልክ እንደ አሉላ እንደ ባልቻ አባነብሶ  ይዘመርላችኋል ታሪክም በከበረ ቦታ ላይ ያስቀምጣችኋል።  

በሃገራችን ሌላው በአደገኛ የእልህ ማእበል ውስጥ እየነጎደ  ያለው ትልቅ ሃይል ወጣቱ ነው። እንደሚባለው ከሃገራችን ህዝብ ከ70% በላዩ በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ነው፤ ይሄም ማለት ባብዛኛው በወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን የተወለደ ማለት ነው፤ ከዚህ ክፍል ውስጥ በስራ ላይ ያለው 20% እንኩዋን ለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ይህ ወጣት ያደገው ኦሮሞ ነህ፤ ትግሬ ነህ፤አማራ ነህ ፤ ሲዳማ ነህ ወዘተ ወዘተ እየተባለ ነው። ኢትዮጵያዊነት እንደነገሩ ሲወራ ሰማ እንጅ በአያት ቅድመ አያቱ ከፍተኛ መስዋእትነት የተገነባነት ማንነቱ እንደሆነ አልተነገረውም አልተማረውም፤ ተወልዶ  ያደገው “በብሄር” ማንነቱ ነው፤ ከዚህ በላይ ለዚህ ወጣት ምንም የለም፤ ሃገራዊ ማንነትን ትርጉም በደንብ አያውቅም እንዲያውም ኢትዮጵያዊነት ብሄሬ ለሚለው ስብስብ መከራን እና ችግር እንዳመጣበት ተደርጎ ሲቀሰቀስ ያደገ ትውልድ ነው። ፍትህ ማጣቱ ስራ አጥነቱን ችግሩና መከራው የመጣበት ከገዠዎቻችን ባህሬ እና ደካማ አስተዳደር መሆኑ ቀርቶ ከኢትዮጵያዊነት ትስስሩ እንደሆን ተደርጎ ለረዥም ጊዜ ተቀስቅሷል፤ ኢትዮጵያዊነት ያዋረደው እና ያሳነሰው እንደሆነ ተደርጎ ተምሮታል፤ ከዚህም አልፎ የሌሎች “ብሄሮች” ተወላጆች መጤዎች ጠላቱ እንደሆኑ ተደርጎ ከልጅነቱ ጀምሮ ተቀስቅሷል። አሁንማ ይህን ሁሉ አልፈው እነሱ የማያመልኩት አምልኮት ሁሉ አጥፍያቸው እና ጠላታቸው እንደሆነ አድርገው በማቅረብ በጣም አደገኛ አቅጣጫ እያስያዙት ነው፤ የብሄር ድርጅቶቹ መሪዎች እና “ብሄርተኛ” ነን የሚሉ አክቲቢስቶች ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ድርጅታዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ወጣቱን በዚህ መልክ ሲቀርጹት በመቆየታቸው በዚህ የተዛባ ስለ ልቡና ያደጉት ወጣቶች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ መጥተዋል።  በየቦታው ሽብር መፍጠር ሰውን በግፍ መግደል የህዝብ እና የሃገር ንብረት ማውደም የእምነት ቦታዎችን ማቃጠል እንደ ጀግንነት ይቆጥሩታ። በዙርያቸው ባለው ባልተደራጀው ህብረተሰብ ላይ በሚፈጽሙት አስነዋሪ ስራ “ብሄራቸውን” ታላቅ ያደረጉ ይመስላቸዋል፤ ሌላውን ስላዋረዱ እና ስላጠቁ የብሄር አቅማቸውን ያሳደጉ ይመስላቸዋል፤ “ብሄራችን” የሚሉት ክፍል በዚች አገር ግንባታ ላይ ያደረገውን በጎ እና የሚያኮራ አስተዋጽኦ እያዋረዱት እንደሆነ ቢነገሩም አይሰሙም፤ባላቸው የእውቀት ማነስ ምክንያት እንኳንስ የወገኖቻቸውን እና የሃገራቸውን የራሳቸውንም የወደፊት እጣ ፈንታ አያውቁም፤ በደመ ነብስ በትንሹ ሲለኩሱዋቸው በትልቁ ያግለበልቡታል አንዳንዴ የሚጓዙበት የጥፋት ጎዳና “ብሄራችን” ለሚሉት ቡድን የጀግንነት ታሪክ የሚያስጽፍ እንደሆነ አድርገው ስለሚቀሰቅሱዋቸው “ብሄሬ” የሚሉትን ህብረተሰብ ምን ያህል እያዋረዱት እና እያሳፈሩት እንደሆነ አይታያቸውም ። ይህም ሁሉ ሲሆን ከፍተኛውን መስዋእትነት የሚከፍሉት ወጣቶቹ ናቸው፤ ቀስቃሾቹ ህይወት በሚጠይቀው ቦታ ላይ አይገኙም  ወጣቶቹን ግን የእውቀት ሳይሆን የእልህ ትጥቅ አስታጥቀዋቸዋል። ይህ የእልህ መንገድ በተሳሳተ አስተምሮ የተገነባ በመሆኑ ወጣቶቹ ላይ መፍረድ ቢያስቸግርም  ዝም ተብሎ ግን ሊታይ አይገባውም። እነዚህን ወጣቶች መስመር በማስያዝ ከአፍራሽነት ወደ ገንቢነት ለመለወጥ ከፍተኛ የማስተማር ስራ ይጠይቃል፤ ይህን ደግሞ ማድረግ ያለባቸው ሙህራን ናቸው (መንግስት እና የሃይማኖት መሪዎች ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ባለመዘንጋት) ታዲያ ምሁራኖቻችንስ አገራችን ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ምን እያደረጉ ነው በዚህ ዙሪያስ ያላቸው ብቃት እና አስተዋይነት ምን ያህል ነው የሚለውን ደግሞ ትንሽ ልዳስስ።

በመጀመርያ ያገራችን ሙህራን በሰፊው የከፋፈለው እና ሃገራችን የተፈታተናትን የ “ብሄር” ምንነትን ትርጉም ካለንበት ዓለማቀፋው እድገት እና ማህበረሰባዊ ትስስር አንጻር ስናይ በሃገራችን የፈሉት “ብሄርተኛ” መሪዎች እና ምሁራን የብሄርን ምንነት ሊኖረው ከሚገባ ማህበራው እና  ፖለቲካል ትስስር ወደ ኋላ ጎትተው ethnic groupን እንደ ብሄር መገለጫ በማድረግ ይጠቅመናል ብለው ያቀነቀኑትን የጆሴፍ እስታሊንን ትንተተና  እንኩዋን የማያሟላ  የግብዞች ንድፈ ሃሳብ ሆኖ  እናገኘዋለን። ጆሴፍ እስታሊን በሰጠው ትንተና አንድ ህዝብ እንደ አንድ  ብሄር ለመታየት ቢያንስ በቋንቋ፤በባህል፤በማህበራዊ ትስስር፤በኢኮኖሚ ትስስር እና በመልካ ምድራዊ አቀማመጡ የፈጠረለት ማንነት እንደሆነ ይገልጸዋል። በዚህም ንድፈ ሃሳቡ በወቅቱ ደንበራቸው በግልጽ የሚታወቅ የራሳቸው ማንነት እና የተለየ ታሪክ የነበራቸው ግዛቶች በወቅቱ የነበረው ርእዮታለማዊ አንድነት አገናኝቷቸው ሉዓላዊነታቸውን በማጠፍ የሶቤት ህብረትን ለመመስረት የተቀላቀሉትን 17 የሶቤት ህብረት ግዛቶች መብት የሚያከብር የፖለቲካ ፍልስፍና ሃሳብ ነበር እንጅ እንደኛ ቅጥ አንባሩ በጠፋው አሰፋፈር የተቀመጠውን ህዝብ የሚያጨራርስ እውር ትንተና አልነበረም። እነዚህ የሶቤት ህብረት አካል ሆነው ብሄራው ማንነታቸው የታወቀላቸው ህዝቦች ወደ ሶብየት ህብረት የተቀላቀሉት ብዙዎቹ በድርድር ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ በተባበሩት መንግስታት ከነሰንደቅ አላማቸው እውቅናቸውን እንደያዙ ቆይተው ነበር፤ ለዚህም ምሳሌ ዩክራይን ማስታወስ ይቻላል። ወደኛ አገር ስንመጣ  ግን እንደ ጀርመን እንደ ጣልያን እንደ ራሽያና ሌሎችም ቀደምት አገሮች በነበረው የሃገር ግንባታ ሂደት አንዱ ንጉስ በሌላው ንጉስ ላይ በመዝመት ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት ለመመስረት ብዙ ጊዜ ፈጅቶብናል፤ በተካሄዱት ጦርነቶችም በህዝቡ ላይ ብዙ ጉዳቶች ደርሷል። ይህ ማለት ግን አንድ ወጥ ነን ማለት አይደለም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ የተለያየ ባህል እና ወግ ያላቸው ወገኖች ነበሩ፤ በሂደት ግን አንዳንድ ቋንቋዎች የበለጠ እየተስፋፉ መጥተው አንዳንዶቹም ተውጠው ዛሬ ካለንበት ደረጃ ደርሰናል። ዛሬ ባለንበት ደረጃ ደግሞ “ብሄራችን” ብለው በሃሳባቸው በሚከልሉት ክልልም ሆነ በወያኔ እና በኦነግ ሙህራን በተነድፈው አከላለል የብሄርን ምንነት የሚያሟላ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም። መቼም በግልጽ እንነጋገር ከተባለ የኦሮሞን ህዝብ እንኳን ብናይ ብዙ ልዩነቶችን እናያለን እንደ ምሳሌ ባህልን እንኳ ብናነሳ የሽዋ ኦሮሞ ወይም የወለጋ ኦሮሞ ባለባበሱ በአበላሉ በአኗኗሩ ከሀረር ኦሮሞ ጋር ፍጹም ግንኙነት የለወም፤ አሁንም የኦሮም አክቲቢስቶች ካልተቆጡ የሽዋ ኦሮሞ ስለንቦናዊ አንድነቱ ከሽዋ አማራ ጋር እንጅ ከሀረር ኦሮሞ ጋር አይደለም የኢኮኖሚ ትስስሩ መልካምድራዊ አሰፋፈሩ እና ሌሎችም ልገልጻቸው የማልፈልጋቸው ነገሮች የተባለውን “ብሄር” መመዘኛ ለማሟላት የሚበቁ አይደለም። የሀረር ኦሮሞ ከወለጋ ኦሮሞ ጋር በአንድ መንግስት ጥላ ስር የኖረው በኢትዮጵያዊነት በሚያስተዳድሩ መንግስታት ስር እንጅ ከዚያ በፊት በኦሮሞነት የጋራ አስተዳደር ኑሮውቸው አያውቅም። ይህን ስል ግን በኢትዮጵያ ኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገር ትልቅ ህዝብ እዳለ እየዘነጋሁ አይደለም፤ እኔ ይህን ነጥብ ሳነሳ ባለፉት 50 አመታት “የብሄር ጥያቄ” በሚል ጽንሰ ሃሳብ ምክንያት የተለያዩት ሙህራን የተለያየ አቁዋም ይዘው በሄዱት የተሳሳተ ግትር አቋም ምን ያህል መስዋእትነት እንደተከፈለ ለማሳየት ነው። ቢያንስ ይህን ሁሉ መስዋእትነት ከከፈልን ቦኋላ እነዚህ ፖለቲከኞች ወይም ሙህራን ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ህዝብን በሚጠቅም አገርን በሚገነባ ስራ ላይ ቀሪውን ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ግድፈቶቻችን ለማሳየት ነው። አንዳንድ የኦሮም ፖለቲከኞች እና ሙህራን ከዚህ በፊት የተከተሉት የፖለቲካ መስመር እና የነበራቸው አቋም በሃገርም በህዝባቸውም ላይ ጉዳት እንዳስከተለ በአንዳንድ መድረኮች ቢናገሩትም ወደ ኦሮሞ ህዝብ በተለይም ወደ ወጣቱ ቀረብ እያሉ ይህን ስህተት በማስረዳት ህዝባቸውን ወደ ተስተካከለ የፖለቲካ መስመር ሲመልሱ አይታዩም፤ ይልቁንም ወጣቱ እነሱ ባስጨበጡት የተሳሳተ መንገድ እየነጎደ ከፍተኛ ስህተት ሲሰራ አሁንም የወጣቱን ድጋፍ ላለማጣት የተምታታ መግለጫ ሲሰጡ ይሰማሉ።

 ዛሬ በአለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አሳፋሪ ድርጊት የሚፈጸመው በኢትዮጵያ ዩንበርሲቲዎች ውስጥ ነው፤ ተማሪ ተማሪን ይገላል ተማሪ ተማሪን ከግቢ ውጡልኝ ብሎ በመስኮት ይወረውራል በጩቤ ይወጋል አሳፋሪ ታሪክ። በ60ዎቹ በዩንበርሲቲው እና በኮሌጆች ብቻ ሳይሆን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ለዴሞክራሲ እና ለህዝብ እኩልነት ተማሪዎች ታገሉ መስዋእትነትም ከፈሉ አሁን ግን ሙህሮቻችን ከክልላችን ውጡ የሚሉ ጉዶችን  አፍርተውልናል፤ ዛሬ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች እንደድሮው በአርቆ አሳቢነት በአላማ ሳይሆን የሚቧደኑት በቋንቋ እንዲሆን መምህሮቻቸው ያስተምሩዋቸዋል። አንዳንድ ሙህር ተብለው ለቃለመጠይቅ የሚቀርቡ የዩንበርሲቲ መምህራን ከቀበሌው ካድሬ ያነሰ ትንተና ሲያቀርቡ ስንሰማ እናፍራለን፤ ከሙህራዊ እውቀታቸው ይልቅ “የብሄሬ”  ለሚሉዋቸው የፖለቲካ መሪዎች ያላቸውን ታማኝነት ለመግለጽ ሲሉ የሚቀባጥርቱን አሳዛኝ ትንተና ወይም አስተያየት በሰማን ቁጥር በሃገራችን ተስፋ ለመቁረጥ ይዳዳናል፤ እነዚህ ሰዎች የሚያስተምሩዋቸው ልጆች ይህን ስህተት ቢሰሩ ለምን ይገርመናል እነዚህ ሰዎች ያስተማሩዋቸው ልጆች የሃገር መሪዎች ሲሆኑ ሃገር ወደየት አቅጣጫ እንድትሄድ እንጠብቃለን፤ በሃገራችን ያለውን የሙህርነት ዝቅጠት በቀላሉ የሚታከም አይደለም። ይሄን ስል ቁጥራቸው ይነስ እንጅ በቅንነት እና በብስለት በሙህራዊ ብቃታቸው የሚያኮሩ የሉም ማለቴ አይደለም፤ ያውም በማንም  ውርጋጥ እየተሰደቡ ለኢትዮጵያ እና  ለህዝብዋ ትክክለኛውን የእድገት እና የእኩልነት መንገድ ለማመላከት የማይሰለቹ የቁርጥ ቀን ልጆች አልጠፉም፤ ግን ምን ያደርጋል  በተቃራኒው የቆሙት ሃይሎች መድረኩን በሰፊው ስለያዙት በቂ መድረክ እንዳያገኙ ተደርጓል፤ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ተጽእኖ  ፈጣሪዎቹ “ብሄርተኛ”  ነን የሚሉት ሃይሎች በመሆናቸው ሃገራዊ ራእይ ፈተና ላይ ወድቋል። እንግዲህ መንግስት አርቆ የሚያስብ ከሆነ፤  መንግስታዊ ህልውናውን የሚፈልግ ከሆነ፤ መንግስት የሃገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚያሳስበው ከሆነ፤  መንግስት የወጣበትን ህብረተሰብ የሚወድ ከሆነ፤ መንግስት ከዚህ በፊት ከከሸፈባቸው መሪዎች ታሪክ የሚማር ከሆነ፤ በአጋጣሚ ከጃቸው የወደቀውን ታሪካዊ ሃላፊነት በታሪክ እንዳያስጠይቃቸው ከልህ እና ከማን አለብኝነት ተላቀው ሃገራዊ ራእይ ያላቸውን ሙህራን ድጋፍ በመስጠት ብዙ ስራዎች ሊያሰሩዋቸው ይችላሉ። የግድ የድርጅት አባል መሆን የለባቸውም ለሃገር እና ለሁሉም  ህዝብ የሚጠቅም ሃሳብ እስካላቸው ድረስ ድረስ ሰፊ እድል እና ሰፍ መድረክ ብዘጋጅላቸው የሚያስገኙት ውጤት ክፍተኛ ይሆናል፤ ሙህራኑም ይህን ያልተወጣችሁትን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት የመንቀሳቀስ ሃላፊነት አለባችሁ፤ ማኩረፉ እና ከሌላው አቅጣጫ ወይም ከመንግስት መጠበቁ አያዋጣም፤ ሃገሪቱ የሁላችንም ናት፤ ማንም ቀስቅሶን ወይም ደግፎን ሳይሆን ህሊናችን አስገድዶን ሃልፍነታችን እንድንወጣ ከዚያች መሬት መፈጠራችን ያስገድደናል።