አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር 16፣2012

በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ መንግስታቸው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ የየመን አምባሳደር አምባሳደር ያህያ አልአርያኒ ገለጹ።

አምባሳደር ያህያ ”የየመን መንግስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተመለከተ ወደ ኢትዮጵያ በሰላም እንዲመለሱ አስፈላጊው ጥረት እያደረገ እንደሆኑንና ዜጎችም ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው” ብለዋል።

ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እና ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከ800 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያውን ስደተኞች ወደአገራቸው የሚመለሱባቸውን የተለያዩ አማራጮች እንዲፈልግ ከኢትዮጵያ በኩል ጥያቄ እንደቀረበ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት የየመን መንግስት ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄውን እንዳቀረበና የየመን የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ጉዳዩን እንዲከታተልና ሌሎች አማራጮች ለማየት ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው አምባሳደር ያህያ ያስረዱት።

”በየመን ያለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ የምናደርገው ጥረት ላይ ጫና እየፈጠረ ነው” ያሉት አምባሳደሩ፤ በአገሪቷ ያለው ችግር በሚፈለገው ደረጃ ስራዎችን ማከናወን እንዳላስቻለ ገልጸዋል።

የየመን መንግስት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን እንግልት እንዳይደርስባቸው እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

”ኢትዮጵያውያን የየመን ስደተኞችን በር ከፍተው እንደተቀበሉት እኛም ለኢትዮጵያውን ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እናደጋለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያና የመን በደም የተሳሰረና ለዘመናት የቆየ ትስስር እንዳላቸውና የትኛውም አይነት ችግር የሁለቱን አገሮች ህዝቦች እንደማይለያያቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሁን በየመን ያለውን አለመረጋጋትና ጦርነት የመኖች በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን በየመን ካለው ወቅታዊ መንግስት ጎን ሆና ለምታደርገው ድጋፍና የመኖች ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ ለምታደርገው ጥረት አምባሳደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።