አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር 16፣2012

ትህነግ/ህወሃት ህልውናችን ከኢህአዴግ መዋሃድ አሊያም መፍረስ ጋር የተሳሰረ አይደለም፤ ብዙ አማራጭ አማራጮች አሉን በሚል ርዕስ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ህወሓት የኢህአዴግን የውህደት አጀንዳ በስራ አስፈፃሚውና ማእከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ያልተቀበለው ቢሆንም የመጨረሻ የሚታወቀው በቅርቡ በሚጠራው የህወሓት ጉባኤ ላይ ነው ሲሉ የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እንዳሉት ህወሓት ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የውህድ ፓርቲ ጉዳይ አጀንዳ እንዲሆን አልፈለገም ነበር፡፡

ኢህአዴግን ውሁድ ፓርቲ እንዲሆን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በርካታ የሕግና የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ጥሰቶች ያሉበት ያሉት የህወሓት መሪ ዶክተር ደብረፅዮን “አካሄዱ ኢህአዴግን ውሁድ ፓርቲ ማድረግ ሳይሆን በስመ ውህደት አዲስ ፓርቲ የመፍጠር ነው” ብለውታል፡፡

ከውሳኔው በኋላ ከኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ዶክተር አብይ አሕመድ ጋር ውይይት ተደርጎ “የውህደት አጀንዳው ደግመን እንድናየው ጥያቄ ቀርቦልን ነበር” የሚሉት ዶክተር ደብረፅዮን በህወሓት በኩል ግን የአቋም ለውጥ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

በመግለጫው ዙሪያ የአረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አብረሃ ደስታ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው በሰጡት አስተያየት መግለጫው የህወሃት ተደጋጋሚና የተሰለቸ አካሄድ የታየበት ነው ብለዋል፡፡

አቶ አብርሃ ውህደቱን ላለመቀበል ሲል የሚጣረሱና ውሸታም የሚያስብሉ ምለሾች በተደጋጋሚ ከህወሃት መደመጡን የገለጹ ሲሆን ባለፈው ህወሓት “አልወሃድም” የሚል መግለጫ ማውጣጡንና አሁን ደግሞ “ውህደቱን በጉባኤ እንወስናለን” እያለ ነው ሲል አስታውሰው ስራ አስፈፃሚው “አንወሃድም” ብሎ ቢወስን ኖሮ አስቸኳይ ጉባኤ መጥራት ለምን አስፈለገ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮች አስቸኳይ ጉባኤ ጠርተው እያስወሰኑ ያሉት በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ለመወሃድ ስለተስማሙ ነው ሲሉም አክለዋል።