አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 19፣2012

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ጋር ሲያካሂድ የነበረው ውይይት ባለመግባባት መበተኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በምርጫ ማስፈጸሚያ ሕጉ ዙሪያ ዛሬ ማካሄድ ጀምሮት የነበረው ውይይት ባለመግባባት መቋረጡን በስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ውይይቱ ሊቋረጥ የቻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ አዋጅ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት ረቂቁ ላይ የሰጡት አስተያየት ግብዓት ሆኖ አላገለገለም የሚል ሃሳብ ስላላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

”በመሆኑም የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ አዋጅ ለማስፈጸም በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ከመወያየታችን በፊት በአዋጁ ላይ ያነሳነው ጥያቄ ሊመለስልን ይገባል” ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱኳን ሚደቅሳ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ቦርዱን የሚመለከት ጉዳይ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም እንደ ተቋም የአዋጁን ማስፈጸሚያ ደንብ ማውጣትና መተግበር ስለሚያስፈልግ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ባለድርሻ አካላት በረቂቁ ላይ ሃሳብ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አባላት ”ከዚህ በፊት በአዋጁ ረቂቅ ላይ የሰጠነው ሃሳብ ግብዓት ሆኖ ባለማገልገሉ አሁን በዚህ ደንብ ላይ የምንሰጠው አስተያየት ግብዓት ይሆናል የሚል እምነት የለንም” ብለዋል።

በዚህ የተነሳም ለግማሽ ቀን ተጠርቶ የነበረው መድረክ ያለ ስምምነት ተበትኗል።

የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱኳን ሚደቅሳና ሌሎች የቦርዱ አባላት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሌላ ጊዜ ለውይይት ተዘጋጅተው እንዲመጡ አሳስበው፤ ያላቸውን ጥያቄ በጽሁፍ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

ረቂቅ ደንቡ ፓርቲዎቹ ተወያዩበትም አልተወያዩበትም መጽደቁ ስለማይቀር ለፖለቲካ ሂደቱ ስኬት ሲባል ቢወያዩበት የሚመረጥ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ከዚህ ቀደም ከ 70 በላይ የሚሆኑ ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች የተዘጋጀው ረቂቅ አፋኝ ነው በማለት ሲቃወሙ እና ተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጡ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።