አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 19፣2012

በወልቂጤና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሳይስተጓጎል መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደጀኔ አየለ እንዳሉት የሚመሩት ተቋም በአሁኑ ወቅት በሰላማዊ ሁኔታ የመማር ማስተማሩን እያካሄደ ነው፡፡

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ናሆም ጀምስ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በመደበኛው መርሃ ግብር 7 ሺህ 500 ተማሪዎችን እያሰተማረ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የነበሩ ችግሮችን መነሻ በማድረግ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምግብ ቤት ችግር ለመፍጠር ተሞክሮ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር በማዋል የትምህርት ሂደቱ ሳይስተጓጎል መቀጠሉንም ጠቅሰዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረም አባላት ችግር የሚፈጥሩ ስጋቶችን ለአመራር በማሳወቅ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑንም ፕሮፌሰር ደጀኔ ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ችግር ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን እንደማይታገስና ከዚህ ቀደም በነበሩ የትምህርት ዓመታትም ችግር ለመፍጠር በሞከሩ ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አንስተዋል።

“አብዛኛው ተማሪ ሰላም ወዳድና ትምህርቱ ላይ የሚያተኩር ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ደጀኔ፤ ችግር የሚፈጠረው “የራሳቸውን ዓላማ ማስፈፀም የሚፈልጉ ኃይሎች” በሚያደራጇቸው ጥቂት ግለሰቦች ነው ብለዋል።

ተማሪዎች ለአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ሰላም መጠበቅ ቀዳሚውን ሚና እየተወጡ ነው ያሉት ዶክተር ናሆም፤ የዩኒቨርሲቲው አመራር “እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት” ድረስ የተማሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች ችግር ከተፈጠረ በኋላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጡ የገለጹት ፕሮፌሰር ደጀኔ፤ መንግሥት የደህንነት አሰራሩን በማጠናከር ችግር ፈጣሪ ኃይሎችን ቀድሞ መቆጣጠር እንደሚገባ አንስተዋል።

“መንግሥት ችግር ለመፍጠር ከሚሰሩ ኃይሎች አንድ እርምጃ ቀድሞ ይገኝ” የሚሉት ፕሮፌሰር ደጀኔ፤ እኩይ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦች በመታወቂያ አጭበጭብረው እንዳይገቡ የዩኒቨርሲቲው ጥበቃዎችም ተማሪዎችን መላመድ ና በዕይታ መለየት ይገባቸዋል ነው ያሉት።