አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 19፣2012

ሕወሓት፤ ብልፅግና ፓርቲ በ2012 እንደሚደረግ ከሚጠበቀው አገር ዐቀፍ ምርጫ በፊት ከተመሰረተ ኢትዮጵያ በባለ አደራ መንግሥት መመራት አለባት አለ፡፡

ከቀናት በፊት ሊቀመንበሩ ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲን መመስረቱም ሆነ ኢሕአዴግን የማፍረሱ ሒደት ሕጋዊ መንገዱን አልተከተለም በሚል ኢትዮጵያ ከምርጫ በፊት በባለ አደራ ልትመራ ትገደዳለች ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ኅዳር 18 ምሽት በትግራይ ቴሌቪዥን ቆይታ የነበራቸው የሕወሓት እና ኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ጌታቸው ረዳ ይህንኑ ሀሳብ ደግመውታል፡፡

ኢሕአዴግ አራቱን ብሔራዊ ድርጅቶች የማፍረስ ስልጣን አልተሰጠውም የሚሉት ጌታቸው፤ በሐዋሳው ጉባኤ ሀላፊነቱ ተሰጥቶታል የሚባለው ውሸት ነው ሲሉ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል፡፡

‹‹ብልፅግና ፓርቲ ውኅድ ሳይሆን አዲስ ፓርቲ ነው በማለትም›› ብልፅግናን መስርተው አሁን ባለው የመንግሥትነት ቦታ እንቀጥላለን ካሉ፤ ያን ጊዜ ሕግ የሚፈታው ጉዳይ ይሆናልም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ ኢህአዴግን መውረስ አይችልም፤ የብልፅግና ፓርቲ እየሄደበት ያለው ሂደትም ጨፍላቂ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

በአንጻሩ ብልፅግና ፓርቲ ሕጋዊ ሂደቶችን ተከትሎና ኢሕአዴግን አዋኅዶ እየተፈጠረ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚናገሩት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዐቢይ አሕመድ፤ አዲሱ ውህድ ፓርቲ እውነተኛ ፌደራሊዝምን የሚተገብር እንጂ ጨፍላቂ አይደለም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡