አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 19፣2012

ባለፈው አንድ ዓመት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች ውስጥ በመንግሥት እና በተቋማት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እየተጠናከሩ መጥተዋል።

የመንግሥት ኃላፊዎች የጥቃቱ ዋነኛ ዒላማ ይደረጉ እንጂ፤ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች፣ ሰላማዊ ሰዎችና የውጪ አገራት ዜጎች ጭምር የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

የክልሉም ሆነ የየአካባቢዎቹ የመንግሥት ባለስልጣናት ለግድያዎቹ ተጠያቂ የሚያደርጉት “ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂ ኃይሎችን” ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ከኦነግ ተነጥሎ የወጣውን ‘ኦነግ ሸኔ’ የተባለውን ቡድን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ ከኅዳር 2011 እስከ ኅዳር 2012 ባሉት 12 ወራት ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች በጥቃቶቹ ሰለባ የሆኑትን ሰላማዊ ሰዎችን ሳይጨምር በመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርተው በታጣቂዎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ10 በላይ እንደሚሆን የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ባለንበት ዓመት በዚህ የኅዳር ወር ብቻ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 5 የመንግሥት ባለስልጣናት ተገድለዋል።

የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ ፤ የመንግሥት ኃላፊዎቹ የተገደሉት “ባልታወቁ ታጣቂዎች” ነው ብለዋል።

ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ዕሁድ አመሻሽ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ዞን ኃላፊ የነበሩት አቶ ገመቺስ ታደሰ በታጠቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።

የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አበበ ተካልኝ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ የተገደሉት መስከረም 7 ቀን 2012 ሲሆን ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም የደምቢዶሎ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ገመቹ  በጥይት ተመትተው ቆስለው በህይወት ተርፈዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት የጸጥታና ከተለያዩ የመንግሥት አካላትን ያካተተ የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ እንደነበር ይታወሳል።