አባይ ሚዲያ ዜና -ህዳር 20፣2012

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ድርጅትን በሚመለከት የተሳሳተ ዘገባን አሰራጭተዋል ላላቸው የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር በዛብህ ደምሴ፣ ዜናውን ላስተላለፈው የኢትዮጽያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና ለኢትዮጲያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ዶ/ር በዛብህ ንጉሴ ከመኢአድ ስልጣን የወረዱ ቢሆንም የድርጅቱን ማህተም ይዘው በመሰወር፣ ይሰሩበት የነበረውን ቢሮ ቆልፈው በመጥፋታቸውና ያሉበትን የፖለቲካ አቋም ግልጽ ሳያደርጉ ያለአግባብ መኢአድ ከኢዜማ ጋር ተዋሀደ የሚል ቃለምልልስ መስጠታቸው አግባብ አይደለም፤ የህግ ጥሰትም ነው ብሏል መኢአድ።

ይህን ተከትሎም ዶ/ር በዛብህ የሰጡትን የሀሰት መግለጫ እንዲያስተባብሉና ድርጅቱን ይቅርታ እንዲጠይቁ በማለት ይህ ካልሆነ በህግ እንደሚጠይቃቸው ገልጿል።

ከአቻ ፓርቲዎች ጋር ለፖለቲካ ስልጣን የሚወዳደረው ፖርቲያችንን ስምና ዝና ለማጠልሸትና ለማጉደል፣ ከፓርቲያችን የተሰናበቱትንና በሌላ ምክንያት እንዲኮበልሉ የተደረጉትን ሰው ከኛ ጋር ተቀላቀሉ ብሎ በሚዲያ ማስነገር ተጠያቂ ያደርጋል በማለት ኢዜማን አስጠንቅቋል።

ኢዜማ የራሱን ስም ከፍ አድርጎ ሌሎችን ማኩሰስ፣ አባላትን በጥቅም አታሎ መውሰድና ግለኝነት ህወሓት ኢህአዴግ በፖርቲዎች ላይ ደቅኖት ከነበረው ስጋት የማይተናነስ ነው ብሏል መኢአድ።

በመሆኑም ያሰራጫችሁትን የሀሰት መረጃና ቅስቀሳ ማስተካከያ እንድታደርጉና ድርጅታችንን ይቅርታ እንድትጠይቁ፤ ይህ ካልሆነም በህግ ለመጠየቅ እንገደዳለን ሲል የመኢአድ የማህበራዊ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ለገሰ ወልደሀና ገልጸዋል።

ኢሳት ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ. ም “መኢአድ እና ኢዜማ ተዋሀዱ” በሚል ያሰራጫችሁት መረጃ ትክክለኛነትን፣ ተጨባጭነትንና መርህን ያልተከተለ በመሆኑ ብሎም መኢአድን ሳታናግሩ በመስራታችሁ ድርጅታችን ተጎድቷል ይላል ለኢሳት በተላከው የማስጠንቀቂያ ጽሁፍ።

አቶ ለገሰ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል እንደተናሩት ዘገባው ሆን ብሎ ድርጅታቸውን ለመጥቀምና ሌላኛውን ለመጉዳት እንጅ በስህተት የተሰራ ነው ብለን አናምንም ብለዋል።

በመሆኑም ኢሳት ያጠፉውን የድርጅታችንን ስም ካላደሱና ይቅርታ ካልጠየቁ መብታችንን በህግ ለመጠየቅ እንገደዳለንም ብለዋል።