አባይ ሚዲያ ዜና -ህዳር 20፣2012

ደምሕት ለተነሳበት የህዝብ ጥቅምና ደህንነት ሲባል ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ጋር ለመቀላቀል መወሰኑን በይፋ አስታውቋል፡፡

ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ የክልላችንን፣ የህዝባችንን እና የሀገራችንን ሁኔታ ስንገመግምና ስናጠና ከቆየን በኋላ ለየብቻ ተበታትኖ ከመስራት ይልቅ በአንድነት ተባብሮ መስራቱ አስፈላጊ በመሆኑ ህወሓትን የመቃወም ሀሳባችንን በማቆም በትብብር ለመስራት ወስነናል ብሏል፡፡

ፓርቲው እንዳስታወቀው በቀዳሚነትና በዋናነት መታሰብ ያለበት የህዝባችንና የክልላችን ደህንነት በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት የተጋረጠውን አደጋ ለመዋጋት ከህዝባችንና ከህወሓት ጋር በጋራ በመሆን ለመስራት ወስነናል ሲል አስታውቋል፡፡

ደምሕት ለዚህ ውሳኔ የደረሰው የትግራይ ህዝብ ሊሟሉለት ከሚገባው የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶች አንጻር እና በህዝቡ ላይ የተጋረጠውን የደህንነት ስጋት ለመቅረፍ እንደሆነና ተባብሮ ለመስራት በመወሰን እንደሆነ በመግለጫው አብራርቷል፡፡

የድርጅቱ ጸሀፊ ግደይ አሰፋ እንዳሉት ባለፈው አንድ አመት የሀገሪቱን ሁኔታ ሲያጠና ከቆየ በኋላ ከህወሓት ጋር ባለው የአላማ እና የአቋም አንድነት በትብብር ለመስራት የወሰን ሲሆን ይህንን ሀሳብ የሚቃወሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩ ትናንት ለነጻነቱና ደህንነቱ የወጣንለት እና ያደረግነው ትግል የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ልማት በመሆኑ ከህወሓት ጋር ለውጥ ለማምጣት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ለአስራ ስምንት ዓመታት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በመሆን ለትግራይ ህዝብ ነጻነት የብረት ትግል ሳደርግ ቆይቻለሁ ያለ ሲሆን በ2011ዓም በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ ህጋዊ ፖለቲካ ፓርቲነት ፊቱን ማዞሩን ጠቅሰዋል፡፡

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ የአገዛዝ ዘመን ራሱን ለመቻል በርካታ ሙከራዎችን እያደረገ ሲሆን የውህደት ሀሳብን አለመቀበልን ጨምሮ በሌሎች ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሳትፎ አቅሙን እያዳከመ መምጣቱ  የሚታወቅ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በትግራይ የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸውን ለህዝብ የማስተዋወቅ ፍላጎትና መብታቸው በህወሓት እንደተነጠቁ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይስተዋላል፡፡