አባይ ሚዲያ ዜና -ህዳር 20፣2012

የመከላከያ ሚኒስትር እና የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ውህደቱንና የመደመር ፍልስፍናን የማልቀበለው ነው ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ይህንን ጉዳይ አስመልክተው ከአቶ ለማ በማናቸውም የኦዲፒ እና የኢሕአዴግ ስብሰባዎች ላይ ውህደቱንና የመደመር ዕሳቤን አስመልክቶ የልዩነት ሃሳብ አልሰማንም የተለየ አማራጭ ሃሳብም አላቀረቡም ብለዋል፡፡

አቶ ታዬ ደንደአ ስለ ብልፅግና ፓርቲ አመሠራረት ሂደት፣ ፋይዳዎቹና የአቶ ለማ መገርሣ በውህደቱ አላምንም ማለትን አስመልክተው ከSBS አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አቶ ለማ በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ውህደቱ አስፈላጊ እንደሆነና የመደመር ዕሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካም ጠቃሚ ሃሳብ እንደሆነ ተስማምተው ነው ያጸደቁት፤ ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ታዬ ደንደኣ ከዚያም አልፎ አቶ ለማ በኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴና ጉባኤ፣ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ሁሉ የተለየ አቋም አላንጸባረቁም ሲሉ አክለዋል፡፡

በተጨማሪም አቶ ለማ በዚህ መሄድ አለብን የሚል የተለየ አማራጭ ሃሳብም እንዳላቀረቡ አቶ ታዬ ተናግረዋል ።