አባይ ሚዲያ ዜና -ህዳር 20፣2012

ባሳለፍነው ሳምንት ህዳር 12/2012 በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ከሰኔ 15/2012 ጥቃት ላይ ተያይዞ ከተከሰሱት 13 ግለሰቦች ውስጥ ዘጠኝ ተከሳሾች ከክልሉ መደበኛ የጸጥታ መዋቅር ውጪ የአማራ የሰለላ እና ደህንነት ድርጅት (አሳድ) በሚል ቡድን በማቋቋማቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያስረዳው በዚህ መዋቀር ጠላት ተብለው የተፈረጁ ሃይሎች በተለይም ህውሃት እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ለመሰለል እና በአስፈላጊው ወቅት መንግስትን በማዳከም የሃይል እርምጃ ለመውሰድ የስለላ እና መረጃ ደህንነት ስልጠና ወስደው ተልእኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎችን ያቀፈ እንደነበር ያስረዳል፡፡

በተለይም ሁለተኛው ተከሳሽ አስጠራው ከበደ የተባሉት ግለሰብ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሃገሪቱ ውስጥ የስለላ መዋቅሩን ለመገንባት ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ይህንን ተቋም መስርተዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ግለሰቡ በተቋሙ ውስጥ ከሰለጠኑት 100 ግለሰቦች ጋር በመሆን የአማራ ልዩ ሃይልን ልብስ በመልበስ ወደ ከሚሴ በመሄድ ጥቃት ሰንዝረዋል፡፡

በተመሳሳይም ተከሳሹ ሚያዚያ 22/2011 ከጎጃም እና ከጎንደር የተሰበሰቡ ግለሰቦች መተከል ገብተው በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ በማሰብ ከተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ እና ጥይት አመቻችተዋል በሚል አቃቤ ህግ ክሱን አስነብቧል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት በክልሉ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ የጸጥታ ኦፊሰር ሥልጠና አለ በሚል ሽፋን መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ ሞክረዋል፡፡

ሰልጣኞቹንም በአማራ ክልል ዞኖች በቤኒሻንጉል እና በአዲስ አበባ አስታጥቆ መድቧል፡፡

የክስ መዝገቡ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በቀድሞው የክልሉ የሰላም እና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በተመራው ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል የማፍረስ ተግባር የክልሉን ከፍተኛ አመራሮችና የጦር ኢታማዦር ሹሞች ግድያ ላይ ከመሳተፋቸው በተጨማሪ በተቋማቱ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሕዝቡ እንዲሳተፍ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት መንቀሳቀሳቸውን ያትታል፡፡