አባይ ሚዲያ ህዳር 22፣2012

የሲዳማ የክልል ልሁን ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ቀጣይ የክልል እንሁን ጥያቄዎች እንዴት ይሆን የሚስተናገዱት? የሚል አሳሳቢ ሀሳብ መውለዱ አልቀረም፡፡

በደቡብ ክልል በርካታ ዞኖች ክልል መሆን እንሻለን ፣ እንችላለንም ፤ ልክ የሲዳማ ጥያቄ እንደተመለሰው ሁሉ የኛም ሊመለስ ይገባል ፤የሚሉ ጥያቄዎችንና የይገባኛል መብቶችን እያነሱ ነው፡፡

ታድያ በፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን በመስጠት የሚታወቁት ዶ/ር አለማየሁ አረዳ ሲጀመር አለፍላጎታቸው ደቡብ ተብለው መጨፍለቃቸው ነው ይሄን ሁሉ ያመጣው ይላሉ።

“እንደተሰበሰቡ ቢቆዩ ኖሮ መልካም ነበር ፤ ያሉት ዶ/ር አለማየሁ ነገር ግን ኢህአዴግ አንድም የነሱን ውሳኔ ሳያካትት ነበር የጨፈለቃቸው፡፡

ጥያቄውን ለማንሳት ጊዜና ነፃነት ነበር እየጠበቁ የነበሩት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግና ፌደራሊዝም መምህር የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው የሁሉም ብሄር ጥያቄ በህጉ መሰረት ነው መስተናገድ ያለበት ይላሉ።

“ከሲዳማ መማር ብልህነት ነው የሚሉት ዶ/ር ሲሳይ የሲዳማ ወጣቶች ሀምሌ 11/11/11 ብለው የተፈጠረውን እናስታውሳለን ሲሉ ገልጸው አሁንም ማንኛውም ብሄር ክልል መሆን በህገ መንግስቱ መሰረት መብቱ ነውና በመነጋገርና በህግ ማስተናገድ ነው የሚገባው” ብለዋል፡፡

በዶ/ር ሲሳይ ሀሳብ የሚስማሙት ዶር አለማየሁ “ይቺ ድሀ ሀገር ግን የማያልፍላት ኢኮኖሚዋ ያሳስበኛል” ብለዋል ።

“ክልል በበዛ ቁጥር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ይውል የነበረ ብዙ ገንዘብ ለባህል፣ ለቋንቋና ለእሴት ማሳደጊያ ይውላል ያሉ ሲሆን ከሌሎች ክልሎችና ብሄሮች ጋር ያለው ግንኙነት እየተገደበ ይመጣል ይላላል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል ዶ/ር አለማየሁ።

ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ግን ዘላቂው መፍትሄ ህገ መንግስቱን ማሻሻል ነው ይላሉ።

“ህገ መንግስቱን ማሻሻል ዘላቂው መፍትሄ ነው” የሚሉት ዶ/ር ሲሳይ ክልል መሆን የሚያስችል ዝቅተኛ መስፈርት ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡