አባይ ሚዲያ ህዳር 22፣2012

በክልሉ ኢንቨስትመንት፣ ልማት እና የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) ድጋፍ አንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በአትላንታ- ጆርጅያ ተካሂዷል፡፡

ውይይቱ “የአማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሔደው፡፡

በአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና የአልማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ በተመራው ውይይት በአትላንታ እና አካባቢው የሚኖሩ አማራ ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአማራ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመው ግፍ እንዲቆም መሥራት እንደሚገባ፣ ለትምህርት እና ትምህርት ቤቶች ጥራት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ለማሻሻል መሠራት እንዳለበት፣ የሕዝቡን አንድነት በማስጠበቅ ወደ ተባበረ ልማት ማሳደግ እንደሚገባ እና የጣና ሀይቅ ደኅንነት ጉዳይም ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

በውህድ ፓርቲው ውስጥ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዴት እንደሚመለሱም ተወያዮቹ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው በሰጡት ማብራሪያ የህግ ጥሰት የፈጸሙ አካላት የፍትህ ሥርዓቱን ተከትሎ ተጠያቂ መሆናቸው የማይቀር መሆኑን፣ ለዜጎች ደኅንነት መጠበቅም ህጋዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ውህደቱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ በውህድ ፓርቲው እንደ ሌሎች ሁሉ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችም እንዲመለሱ ትኩረት እንደሚሰጣቸው፣ መዋሃድ ማለትም የሕዝቡን ጥያቄዎች ወደ ጎን መተው ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ውህደቱ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለመተግበር የሚያስችል፣ ሕዝብንም የሚያቀራርብ እና በሀገር ጉዳይ ሁሉም የመወሰን ዕድልን የሚሰጥ እንደሚሆንም ነው አቶ ዮሐንስ ያስረዱት፡፡

የጣና ደኅንነት እና ሌሎችም የሕዝብ አጀንዳዎች መፍትሔ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ ለዚህም በትብብር መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አማራዎች ጥቃቅን ልዩነቶችን በማቆዬት የጋራ በሚያደርጉ ትልልቅ አጀንዳዎች ላይ በጋራ መሥራት እንደሚገባም መክረዋል፡፡