አባይ ሚዲያ ህዳር 22፣2012

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ዙር አገር ዓቀፍ ምርጫ ግንቦት 2012 ዓ.ም ታካሂዳለች።

ለአገር አቀፍ ምርጫ እያደረጉ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ከፊሎቹ የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ወስጥ በማስገባት ከዝግጅታቸው ይልቅ “የምርጫ ይራዘም” ሀሳብ ሲያንጸባርቁ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ለምርጫው እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የትዴት ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንደሚገልጹት፤ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚታየው አለመረጋጋት ምርጫ ለማድረግም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ አመቺ ባለመሆኑ በዚህ ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫም ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ብለው አያምኑም።

የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲያቸው የምርጫ ዝግጅት ማድረግ ጀምሯል።

ቀደም ሲል ፓርቲያቸው ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን በተደጋጋሚ መግለጹን አስታውሰዋል።

ይሁንና መንግስት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ ቃል በመግባቱ ፓርቲያቸውም የምርጫ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል።

የአገሪቷን ሰላምና ጸጥታ የማስጠበቁ ሃላፊነት የመንግስት በመሆኑ ጠቁመው፤ ይህን በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ምርጫ በራሱ ለግጭት መንስኤ እንዳይሆን መንግስት የሰላምና መረጋጋቱን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመልክተው፤ ኢዜማ በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ለምርጫው አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

”የ2012 አገራዊ ምርጫ እንደ ቀደሙት ምርጫዎች መሆን የለበትም” ያሉት አቶ ዋሲሁን፤ ምርጫው ከዚህ ቀደሙ የተለየ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የመድረክ ስራ አስፈጻሚ አባልና የኤፌኮ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ፓርቲያቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ ለአገራዊ ምርጫው ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

የነጻነት ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂኔር እንግዳወርቅ ማሞ፤ ፓርቲያቸው በውጭ አገር የቆየ በመሆኑ ለስድስተኛው ዙር ምርጫ ዝግጅቱ አጭር ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።