አባይ ሚዲያ ህዳር 22፣2012

ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችናበድሬዳዋ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶ ህዝባዊ ብጥብጥ ያስከተለ ሲሆን ወደ ማንነትና ሀይማኖት ተኮር ጥቃት ተቀይሮ የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፍና የንብረት መውደም ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡

በመሆኑም ለተከሰተው እልቂት የመንግስት ህግና ስርዓት ማስከበር ፈጣንና መሆን ያለበትን ያህል እንዳልሆነና ለዘብተኝነት የታየበት እንደሆነ በድሬዳዋ ፣ሀረርጌና ዶዶላ ከተሞች የሚገኙና የጥፋት ሀይሎች ያደረሱት ጉዳት የተመለከቱ ነዋሪዎች ሲገልጹ ነበር፡፡

በመሆኑም ዛሬ ላይ ከተሞች ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለሳቸውን ነዋሪዎቹ ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች እንዳብራሩት ከተማዋ አንጻራዊ ሰላም እንደሰፈነባትና መደበኛ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በዶዶላ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችም አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ጠቅሰው ወደ ፊት ግን ዳግም ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ከተሞች በአሁኑ ሰዓት አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባቸው ሲሆን የጸጥታ አካላት ሰላም የማስከበር ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

ባለፈው ጥቅምት ወር በጥፋት ሀይሎች በተደረገው ግድያና ዘረፋ ምንም እንኳን የ86 ሰዎች ህይወት ማለፉን መንግስት እንዳመነ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን  ነዋሪዎች ግን ትክክለኛ እንዳልሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡