አባይ ሚዲያ ህዳር 22፣2012

የተወሰኑ ግለሰቦች የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በፈጠራ ወሬ አገር ሲያተራምሱና ግጭት ሲያቀጣጥሉ እየታየ ዝም ሊባል እንደማይገባ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ገለጹ፡፡

ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ከ100 እና 200 የማይበልጡ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ችግር ሲፈጥሩ ዝም ከተባለ ነገ ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡

እነዚህ ግለሰቦች እውነትነት የሌለው የፈጠራ ወሬ ዜና አድርገው በማህበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጩ የት ሆኖ እንደጻፉትና እንደለጠፉት በቀላሉ መለየት የሚቻልበት ቴክኖሎጂ እያለ ብሄርን፣ ሀይማኖትን፣ ተቋማትንና ግለሰብን ስም ሲያጠፉና ሲሰድቡ ዝም ብሎ መመልከት ተገቢ አይደለም፡፡

አጥፊውን በህግ ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ ሌላውን ማህበረሰብ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው በፌስ ቡክ ቤተክርስቲያን ወይም መስጅድ ተቃጠለ ብሎ የተቀናበረ ፎቶግራፍ ቢለጥፍ ይህን መረጃ የሚያየው ሰው የተለቀቀው ፎቶ ትክክል ወይ ውሸት ብሎ የማጣራትና የመመርመር ግንዛቤያቸው ውስን ስለሆነ ለግጭት መባባስ መንስኤ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ኡስታዝ አህመዲን ገለጻ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ሀይማኖታዊና የብሄር ጸብ ለማስነሳት እየሰሩ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡

ለምሳሌም ከ15 ቀን በፊት በኢሊሌ ሆቴል የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት፣ የእስልምና መምህራን፣ የመጂሊስ አመራሮችና የክርስትና ሀይማኖት ቀሳውስት ባሉበት ምክክሩ የተካሄደ በመሆኑ ብዙ ሚዲያዎች ተገኝተው ዘግበዋል፡፡

ሆኖም ይህንን ህዝባዊ ፕሮግራም የሆነ ሰፈር ያሉ ሰዎች ፎቶ ወስደው “ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የሀይማኖት ሰዎች ባካሄዱት ጉባኤ የኦሮሚያን መገንጠል እንደግፋለን” አሉ ሲሉ አሰራጭተዋል ብለዋል፡፡

የሀሰት ወሬ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩ አካላትን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ያሉት ኡስታዝ አህመዲን “ማንም ሰው ስህተት ከሰራ ማንኛውም ሰው ሊተች ይችላል ግን ፈጥረህ፣ አስመስለህ፣ ፎቶግራፍ አቀናብረህ ታጋይ ነኝ ብለህ ከወጣህ ህግ የለም ማለት ስለሚሆን ሊጠየቁ ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡