አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር 23፣2012

ድምጻዊው ባለፈው እሁድ ከሰዓት በኋላ ገርጂ በሚገኘው አንበሳ ጋራዥ አካባቢ በእግሩ በሚጓዝበት ወቅት ማንነታቸውን በማያውቃቸው አምስት ሰዎች ጥቃቱ እንደተፈጸመበት ተክለ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጨምሮም ጥቃቱን ከፈጸሙበት ሰዎች ጋር ምንም አይነት ንግግር እንዳልነበረና አላማቸው ጉዳት ማድረስ እንደነበረ ገልጿል።

“ምንም አይነት ንግግር አልተናገሩኝም፤ በቀጥታ ወደ ድብደባ ነበር የገቡት” ሲል ተናግሯል።

ከዚህም በመነሳት ከባድ አደጋን ለማድረስ ዕቅድ እንደነበራቸውና ጥቃቱ የታቀደና “በደንብ የሚያውቁኝ መሆን አለባቸው” በማለት ግምቱን አስቀምጧል።

ድማጻዊው በደረሰበት ድብደባ ሳቢያ በቀኝ እጁ፣ በአፍንጫው፣ በጭንቅላቱና የግራ ኩላሊቱ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበትም ለቢቢሲ ተናግሯል።

የገርጂ ፖሊስ ጣቢያ ባልደረባ የሆኑት ምክትል ሳጅን ዮሴፍ ተስፋዬ፣ “አርቲስቱ አለባበሳቸውን ወይም መልካቸውን ማስታወስ የሚችል ከሆነ ተከታትለን ልንደርስባቸው እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።