አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር 24፣ 2012

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት መፈጸም ግልጽ የሆነ የፖሊሲ አማራጭ ለህዝብ ለማቅረብ ዕድል እንደሚፈጥር የሁለት ፖለቲካ ፓርቲ ሊቃነ መናብርት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ህዝቡ ግራ ሳይጋባ የቀረበለትን ግልጽ የፖሊሲ አማራጭ በቀላሉ ለመምረጥ ያስችለዋል።

የፓርቲዎች ውህደት መፈጸም የተሻለ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅምን ከማጠናከር ባሻገር በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳር የተሻለ ስብስብ እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ የሺዋስ ገለጻ፤ የዳበረ የዴሞክራሲ ዕድገት ባለባቸው የአውሮጳና የእስያ አገሮች ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ከሦስት አይበልጡም።

የተለያየ ሀሳብ ያላቸውን ፓርቲዎች ወደ አንድ በማምጣት ውህደት መፈጸም ፈታኝ እንደሆነ የገለጹት አቶ የሺዋስ ፤ የኢህአዴግ እና አጋር ፓርቲዎች ውህደት ሲፈጽሙ ችግር ሊገጥም እንደሚችል ይታወቅ እንደነበር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ከሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቀላሉ ውህደት መፈጸም የቻለው ከዚህ በፊት በኀብረት፣ በአማራጭ ኃይሎች፣ በቅንጅትና በመድረክ ተሰባስቦ በጋራ የመስራት ልምድ ያካበተ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ /መድረክ/ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ የፓርቲዎች ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ መሰባሰብ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ውህደት በስምምነት እንጂ በግዳጅ ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሌለበትም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጠናከር የፓርቲዎች መሰባሰብ አስፈላጊ መሆኑን ፕሮፌሰር መረራ ገልጸዋል።

”በተለይ የፓርቲዎች መሰባሰብ አቅማቸውን በማጠናከር የህዝብ ጥያቄን በአግባቡ ለመመለስ ያስችላል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ107 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል።