አባይ ሚዲያ-ህዳር 26፣2012

በወልቃይት ጠገዴ የአዲረመጥ ከተማ ነዋሪዎች በትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ሚሊሻዎችና ፖሊሶች በሚሰነዘር ጥቃትና ድብደባ ከቀናት ወዲህ ለከፍተኛ ስጋት መጋለጣቸውን ለአባይ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎች በስልክ እንደነገሩን ከትላንት በስቲያ ህዳር 24/2012 በቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ፀጋዬ በርሄ የሚመራ የባለስልጣናት ቡድን ወደ ወልቃይት አዲረመጥ ከተማ በመግባት ከፀጥታ አካላት ጋር ሲመክሩ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

የመረጃ ምንጫችን እንደሚሉት ባለስልጣናቱ ሲነጋገሩበት የነበረው አጀንዳ በዋነኝነት ራሳቸውን ለጦርነት እንዲያዘጋጁ ያለመ እንደሆነ ገልጸው ውይይት ያካሄዱትም ከመረጧቸውና የእኔ ናቸው ከሚሏቸው ሚሊሻዎች ጋር ነው ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ አዲጎሹ ድርኩታን በተባለ አካባቢ ከህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ “የአማርኛ ሙዚቃ አጫውታቹሀል፣ የጭፈራ ባህል አሳይታቹሀል” የተባሉ 40 የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች መታሰራቸው የነገሩን ምንጫችን ባልተገባ ሰበብ ወደ እስር የተጋዙት ወጣቶች በአሳሪዎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና ከመካከላቸው 4ቱ እስካሁን አልተፈቱም ብለዋል።

ወጣቶች ያለ ምክናያት እየታፈሱ እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት በሰላም ወጥቶ ለመግባት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን የሚሉት ምንጫችን በአጠቃላይ በህጋዊ መንገድ ያቀረብነው የወልቃይት አማራ የማንነት ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ የፌደራል መንግስቱ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ የሚገባበትን አግባብ መፍጠርና መብትን ማስጠበቅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡