አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር 26፣2012

ባለፉት ዓመታት ጎንደርና አካባቢዋን ለማወክና የጦር ቀጠና ለማድረግ በርካታ ቡድኖችና ግለሰቦች ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና የቅማንትና አማራን ህዝቦች በማጋጨት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ሲያሟሉ እንደነበር ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ህዝቡን አላስፈላጊ ብጥብጥ ውስጥ ሲገቡ ግለሰቦችና ቡድኖች ተለይተው ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በቅማንትና አማራ ህዝቦች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ በጎንደር እና አካባቢዋ የዕርቅ ስነ ስርዓት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በጎንደር ከተማ የዕርቅ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት በጎንደርና አካባቢው የሚገኙ ህዝቦች ወደ ሰላም መግባት እንዳለባቸውና ቀጣይነት ያለው የዕርቅ ስነ ስርዓት መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል ፡፡

ህዝቡ አገልግሎት እያገኘ ስላልሆነ ወደ ሰላማዊ ስራው መመለስ አለበት ብለዋል፡፡

የዕርቅና የምክክር ስነ ስርዓቱ በሁሉም አካባቢዎች የሚቀጥል እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ በደብረታቦር ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በአንድ ሀገር ውስጥ የአመለካከት ልዩነት መኖር ችግር የለውም ያሉ ሲሆን ችግር የሚሆነውን ተወያይቶ በሠላም መፍታት አለመቻል እንደሆነም አመልክተዋል።

ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን የመሪዎችና የተቋማት ፍላጎት እና ባሕል ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው ለፖለቲካ እና ለሃይማኖት ሽፋን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ማጣላት እንደማይገባም ገልፀዋል።

በግለሰቦች የሚታየው አለመረጋጋት ለሌላው ማኅብረሰብ ችግር እየፈጠረ ስለሆነ በዘረኝነት፣ በጎጥ እና በአጀንዳ የሚነዱ አሉባልታዎች ቆም ብሎ መፈተሽ እንደሚገባም መክረዋል።