አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር፣ 27፣2012

ሰሞኑን ህወሓት ያደረገው ስብሰባ የቆየ ባህሪያቸውን የሚገልጽና አግላይነታቸውን ለማስቀጠል የሚያደረግ ጉዞ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጸዋል፡፡

ትህነግ ህወኃት ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓቱን ማዳን በሚል የፌዴራሊስት ኃይሎች ነን ከሚሉ አካላት ጋር ፎረም ማቋቋም መጀመሩ የትናንት ባሕሪያቸውን የሚገልጽና የቆየውን አግላይነት አካሄድ ለማስቀጠል የሚደረግ ጉዞ መሆኑን አስገንዝበው የብልጽግና ፓርቲ አመሠራረትና የውሕደት ሂደቱ ሕግን የተከተለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አቶ ገዱ ኢሕአዴግ ብቻ ሀገር የሚመራበት ሁኔታ አብቅቶ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያካተተና ኅብረ-ብሔራዊነትን ያከበረ ነው ሲሉም የብልጽግና ፓርቲን ገልጸውታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋ ያሳደሩበት ይህ ፓርቲ አንዳንዶች የትናንት ጨፍላቂነት አስተሳብን ለመመለስ እየሠሩት ያለው ሥራ ተገቢ አካሄድ አይደለምም ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሌሎች እንደሚሉት ሳይሆን ለዘመናት የቆየውን የአካታችነት ችግር ከስሩ የሚፈታ እና አንዱ ተዋናይ እንዱ ተባባሪ የሚሆንበትን የቀረፈ፤ በትብብር የሀገሪቱን ችግር መፍታት እና እውነተኛና የዳበረ ዴሞክራሲን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የብልጽግና ፓርቲ አዲስ የፖለቲካ ባሕል በኢትዮጵያ እንዲዳብር የሚሠራ ቢሆንም ውሕደቱን በጥርጣሬ የሚመለከቱት አካላት መኖራቸው አሁንም ከኢትዮጵያዊ አንድነት ይልቅ በብሔር ስም ቆመው ትናንትን የሚዋጁ በመሆናቸው እውነታውን ሲረዱ በሂደት መለወጣቸው አይቀርም›› ነው ያሉት፡፡

አቶ ገዱ እንዳብራሩት የብሔር ፖለቲካ በጦዘበት ወቅት ይህ ፓርቲ እውን መሆኑ ጥርጣሬ ውሰጥ ያስገባቸው አካላት ተቀዳሚ ተልኳቸው የቀደመውን አካሄድ ለመመለስ የሚፈልጉና በሐሳብ ላይ የተመሠረተ፣ ሁሉን የወከለ ሐሳብ ለማራመድ ፍላጎቱ የሌላቸው አካላት ናቸው ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በውህደቱ ላይ የተቃውሞ ሀሳብ ባቀረቡት አቶ ለማ መገርሳ ዙሪያ ምንም ዓይነት ሀሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡