አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር 29፣ 2012

የሲዳማ ክልልነት በሕዝበ ውሳኔነት መፅደቁን ተከትሎ፤ በደቡብ ክልል የተለያዩ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ተጠናክረው እየቀረቡ ሲሆን እነዚህ የክልልነት ጥያቄዎች ደግሞ አዲስ ሳይሆኑ ከዚህ ቀደም የተነሱና ምላሽ ሳያገኙ በመንከባለል ላይ የሚገኙ ናቸው።

ከሁሉም ጥያቄዎች የሚለየው የጌዲዮ ዞን ጥያቄ ነው የሚሉት የአካባቢው ምሁራንና ተወላጆች በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ ዞኑ በደቡብ ክልል ውስጥ መቀጠል አይችልም ሲሉ ያብራራሉ።

የጌዲዮ ዞን በይፋ የክልል እንሁን ጥያቄውን ለዞኑ ምክር ቤት ያቀረበው ሕዳር 11፣ 2011 ዓ.ም መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል ምክር ቤት የብሔረሰቦች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና በጌዲዮ ዞን ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ ውስጥ የባህል ታሪክና ቅርስ ጥናትና ልማት አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ፀጋዬ ታደሰ የዞኑ ምክር ቤት በክልል እንዲደራጅ፣ የራሱን አስተዳደር መመስረት እንዳለበት ውሳኔውን አሳልፏል ያሉ ሲሆን ይህ ጥያቄ ግን እስካሁን ድረስ ለክልሉ አለመቅረቡን አረጋግጠዋል።

አቶ ጸጋዬ “ከደህዴን የሥራ አስፈጻሚ አካላት ባለው ግፊት የተነሳ የዞኑ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ይህንን ተልዕኮውን መወጣት አልቻለም” ሲሉም አስረድተዋል።

የጌዲዮ ሕዝብ በተደጋጋሚ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን  የገለጹት በዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ታደሰ ኪጤ “ጥያቄው ግን ሲታፈን” መኖሩን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ታደሰ አክለውም የሕዝቡን ጥያቄም ለመንግሥትም ሆነ ለሁሉም አካላት የማቅረብ ሥራው እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

አቶ ጸጋዬ በበኩላቸው ይህ ጥያቄ ለዞኑ ምክር ቤት በይፋ መቅረብ የጀመረው በ2010 ዓ.ም ከዞኑ ውጪ በሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ላይ የደረሰው መፈናቀልና ሞት በክልሉ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ባለመቻሉ መሆኑን ያስቀምጣሉ።

በ2010 ዓ.ም ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የጌዲዮ ማህበረሰብ አባላት መፈናቀልና ያገኘው ትኩረት ማነስ ብቻ ሳይሆን የሕግ የበላይነት ሳይረጋገጥ፣ የተፈናቀሉት ለተራዘመ መከራ መጋለጣቸው ሌላው ምክንያት ነው” ብለዋል።