አባይ ሚዲያ ዜና – ህዳር 29፣ 2012

ኢትዮጵያዉያን ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመወያየት መፍታት አለብን ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሣሕለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።

ፕሬዝዳንቷ 14ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን አስመልክቶ በዛሬዉ ዕለት ባስተላለፉት መልእክት ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመወያየት በመፍታት የጋራ ቤታችንን ኢትዮጵያን መገንባት አለብን ብለዋል።

ስለሀገራችን አንድነት ሲወራ በሚለያዩ፣ በችግሮችና በጎደለዉ ብቻ ሳይሆን ተስፋ ሰጪ በሆኑ ነገሮች ላይም ማተኮር ተገቢ መሆኑን ወ/ሮ ሣህለወርቅ አስምረዉበታል።

ለዚህም የአንዳችን ጥቅም የሁላችን ትንሳኤ፣ የአንዱ መጠቃት የሁላችንም ጉዳት መሆኑንም መረዳት አለብን ብለዋል።

«የሌላዉን መብት ማክበር የራሳችንን መብት ማክበር መሆኑን እንዲሁም የሌላዉን መብት ስንረግጥ ለራሳችን መብት መረገጥ በር እየከፈትን መሆኑን መገንዘብ ያሻል» ያሉት ፕሬዝዳንቷ ያ ሲሆን ብሄራዊ መግባባትና አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን መገንባት ይቻላል ነዉ ያሉት።

ለዚህም ዜጎች በሀገራቸዉ ጉዳይ እኩል ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸዉ አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ለዜጎችን መብት መከበር ከመገፋፋት ይልቅ በአንድነትና በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

አንዱ የበላይ አንዱ የበታች መሆን ኢትዮጵያን ከመበተን ዉጭ ፋይዳ እንደሌለዉም አቶ ሽመልስ አመልክተዋል።

በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረዉ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን «ህገ-መንግስታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሰላማችን›› በሚል መርህ ከትናንት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።