አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 30፣ 2012

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አንድ አመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ለቀረው የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውሰጥ ምላሸ ካልሰጠው ጉዳዩን በአቤቱታነት ወደ ፌዴሬሸን ምክር ቤት እንዲወሰድ የቀረበለትን አጀንዳ የወላይታ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል::

የወላይታ ዞን ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤውን የጠራው የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም እና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ተብሏል::

ጥያቄው የአገሪቱ ህገ – መንግስት በሚፈቅደው መሰረት ለደቡብ ክልል ምክር ቤት የቀረበ ቢሆንም ምክር ቤቱ ግን ጉዳዩን ለአገሪቱ ምርጫ ቦርድ አልመራልንም ይህ ደግሞ አሁን ምክር ቤቱ ለተጠራበት አስቸኳይ ጉባኤ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን የወላይታ ዞን ምክር ቤት አፌ ጉባኤዋ ወ/ሮ አበበች እራሾ ተናግረዋል::

የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ከቀበሌ እስከ ዞን ምክር ቤት ተወያይቶ ታህሳስ 10/2011አ.ም የዞኑ ምክር ቤት በክልል የመደራጀት ጥያቄውን አፅድቆ ውሳኔ አሳልፏል ተብሏል::

በአሰራሩ መሰረት ለክልሉ ምክር ቤቱ ጥያቄው በቀረበለት በ1አመት ጊዜ ውስጥ ማደራጀት የሚጠበቅበት ቢሆንም ጥያቄው ለደቡብ ክልል ምክር ከቀረበ አንድ አመት ሊሞላው 10 ቀናት የቀረው ሲሆን በቀሪዎቹ ቀናት ምክር ቤቱ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት ካልቻለ ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሸን ምክር ቤት በመውሰድ አቤቱታ እንደሚያቀርብ ገልጿል::

ጥያቄው ህጋዊ ሂደቱን ጠብቆ ምላሽ እንዲያገኝ ከክልሉ እና ከፌደራል የመንግስት አካላት ጋር ተደጋጋሚ ምክክር መደረጉን ተገልጿል፡፡

ከቀናት በፊትም የወላይታ ህዝብን የወከለ ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በቤተ- መንግስት ምክክር መድረጉ የሚታወስ ነው::