አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 30፣ 2012

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ጣቢያዎች በሚገኙ ሴቶችና ህጻናት ላይ ስለሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ስፋት፣ መንስኤዎች፣ መከላከል፣ የህግ ማዕቀፎችና ድጋፎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ለአብነትም ከጌዴኦ ዞን፣ ከምዕራብ ጉጂ ዞን እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የመጡ አይነታዊ መረጃዎች ለውይይቱ መነሻነት ቀርበዋል።

በመጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ተፈናቃዮች የተገኙ መረጃዎች እንዳሳዩት ጾታዊ ጥቃቱ እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ባሉ ህጻናት ላይም ጭምር እንደሚፈጸም ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ ተገኝተው የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ወ/ሮ ራሄል እንደገለጹት 20 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ወደ መጠለያ ከመጡ በኋላ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡

በዚህ መነሻም ተወያዮቹ በተፈናቃዮች ዙሪያ የተቀመጡ የህግ ማዕቀፎች፣ የህገ-መንግስት ድንጋጌዎችና የአፈጻጸም ክፍተቶች ላይ መክረዋል።

አሁን ላይ መንግስት የአገር ውስጥ መፈናቀልን ህጋዊ መሠረት ባለው አግባብ ለመቆጣጠርና ለመደገፍ ሲልም ፖሊሲ እያዘጋጀ ሲሆን መፈናቀል ሲኖር ሴቶችና ህጻናት ቀዳሚ ሰለባ መሆናቸውና ወደ መጠለያ ከመግባታቸውም በፊት ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው በዚህ ላይ ሊሰራ ይገባል ነው የተባለው።

ጽሁፍ አቅራቢዋ ወ/ሮ ራሄል አክለውም በወንዶች ላይም ጥቃቱ እንደሚፈጸም ገልጸው በአጠቃላይ በሁለቱም ጾታ ከ66-68 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን  ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ እንደተገለጸውም ዜጎች ሲፈናቀሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰብአዊ እርዳታ ብቻ በመሆኑ ለጾታዊ ጥቃት ትኩረት አልተሰጠውም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከኖርዌይ ቤተክርስቲያን የዕርዳታ ድርጅት ጋር በመተባበር ሴቶች ለሰላም በሚል መሪ ሀሳብ ኮንፈረንስ እያካሄደ ሲሆን ውይይቱ ያስፈለገበት ምክንያትም በግጭት እና መፈናቀል ውስጥ ዋነኛ ተጎጂዎች ሴቶች በመሆናቸው እና የሚፈጠሩ ግጭቶችን በባህላዊ መልኩ የመፍታት ትልቅ ሚና የሚጫወቱት ሴቶች በመሆናቸው ይህን ሚናቸውን እንዲወጡ ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።