አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 30፣ 2012  

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን የሰላም የኖቤል ሽልማት በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ሰልፈኞች በኖርዌይ መዲና ኦስሎ መፈክራቸውን አንግበው ወጥተዋል።

በትናንትናው ዕለት በኖርዌይ የሚኖሩ ኤርትራውያን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሽልማት ለሰጠው የኖቤል ኮሚቴ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም በሚገባ አልተረጋገጠም፤ የኖቤል ሽልማት ሊሰጣቸው አይገባም” በሚልም ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።

ከተለያዩ የኖርዌይና የስዊድን ከተሞች የመጡ 250 የሚጠጉ ኤርትራውያን “በሰላም ስም ሳይታሰብበት ሽልማት ሊሰጥ አይገባም፤ በተግባር እንጂ የወሬ ሰላም አንቀበልም” የሚሉ የታቃውሞ ድምፆችን በማሰማት ወደ መንግሥታዊ ተቋማትም አምርተዋል።

የኤርትራ መንግሥትን በተመለከተ የተለያዩ ስር ነቀል ለውጦች ሊመጡ ይገባል በሚል የሚንቀሳቀሰው በኖርዌይና አካባቢው የሚገኝ የ ‘ይበቃል’ ወይም ‘ይአክል’ ኮሚቴ ለሦስት የመንግሥት ተቋማት ደብዳቤ እንደፃፈ የኮሚቴው ሊቀ-መንበር ቲቲ ኃይለ ለቢቢሲ ገልፃለች።

ቲቲ እንደምትለው፤ ለኖርዌይ መንግሥት በአካል፣ ለኖቤል ኮሚቴ በአድራሻቸው እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ደግሞ በኢሜይል ያላቸውን ተቃውሞ አድርሰዋል።

የይበቃል ኮሚቴ ፀሐፊ ይብራህ ዘውደ፤ ምንም እንኳ ኤርትራና ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ስናይ ወደ ተግባር የተሸጋገረ ነገር እንደሌለ” ይናገራል።

የኤርትራ ሕዝብ የጠበቀውና የተመኘው ለውጥ እንዳልመጣ በመግለፅ፤ በሁለቱም አገራት የሰላም ስምምነት አማካኝነት የተሰጠው የኖቤል ሽልማት ፍትሃዊ እንዳልሆነም አክሎ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ለሁለት አስርት አመታት ተቋርጦ የነበረው የስልክ፣ የበረራ መስመሮች ተጀምረዋል።

ለአጭር ጊዜ ቢሆንም የተዘጉ ድንበሮች ተከፍተው የተለያዩና የተነፋፈቁ ሕዝቦች መገናኘታቸውን ብዙዎች በበጎነት የሚያዩት ተግባር ነው።

ይሁን እንጂ እነዚህ መልካም ጅምሮች እንዳሉ ሆነው፤ በሁለቱ አገራት መካከል በተጨባጭ የመጣ ሰላም አለመኖሩን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊገነዘብ እንደሚገባው ተቃዋሚዎቹ ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከጋዜጠኞች ጋር ሊያደርጉት የነበረው ቃለ መጠይቅ አልሳተፍም ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።