አባይ ሚዲያ ዜና- ህዳር 30፣ 2012  

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ትዴት በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው  የኢህአዴግ አመራር በትግራይ የፈጠረውን የአፈና ስርዓት በሀገሪቱ አንዲያንሰራራ አድርጎ ለብዙ መከራ እንደዳረገንና ወገን ከወገኑ ጋር እንዲጋጭና ደም እንዲፋሰስ ማድረጉ የሚታወቅ ነው ብሏል፡፡

ህወሓት አሁንም ከማህል አገር ኮብልሎ ትግራይ ውስጥ መሽጎ ወደ ፈጠረው የአፈና ስርዓቱ ለመመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል ያለው ትዴት ይህንን የአፈናና የከፋፍለህ ግዛው ስርዓት ተወግዶ የዴሞክራሲ ፣የፍትህ ፣የእኩልነትና የአንድነት ስርዓት ይመሰረት ዘንድ በትግል ላይ ስለሚገኝ ህዝባዊ ትብብርና ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል፡፡

በኢትዮጵያ በተገኘው የለውጥ ሁኔታ ከሰኔ 2010 ዓ.ም ጀምሮ አገር ቤት በመግባት በሰላማዊ መንገድ ዓላማውን ሲያራምድና አባሎችን ሲሰበስብ የቆየው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ምዝገባ በሚፈቅደው መሰረት አንደኛ ጉባኤውን አካሂዶ ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) በመግለጫው የትግራይ ህዝብም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያነሳቸውን የስራ አጥነትና ድህነት፣ የፍትህ ዕጦት፣ የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሙስና፣ የጤና ግልጋሎት ማነስ፣ የትምህርት ጥራት ጉድለት፣የብሄር ጥያቄ፣ የመሬትና የግብርና ጥያቄ እና ሌሎችን የመፍትሄ አቅጣጫ ሊሰጡ የሚችሉ ፕሮግሮሞችን ይዟል ብሏል፡፡

ትዴት በትግራይና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር ፕሮግራምና ዓላማን መሰረት ባደረገ መንገድ በቅንጅት ወይም በግንባር ለመስራት በማዕከላዊ ኮሚቴው የሌላ ውሳኔ ሳይጠብቅ እንዲፈጽም ውሳኔ አሳልፏል ብሏል፡፡

በመጨረሻም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው የመናገር፣ የመጻፍ ፣ የመደራጀት፣መሰብሰብ፣ ነጻ ሚዲያ መብቶች ትግራይ ውስጥ ተከለከለ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ለፍትህ ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለነጻነት፣ ለብሄራዊ እኩልነት፣ ለመልካም አስተዳደር መታገል አለበት ሲል በመግለጫው አትቷል፡፡