አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 1፣2012

የጌዲኦ ዞን የቀጣይ አስተዳደር ምርጫው ከማህበረሰቡ የፈለቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ፤ የህዝቡንም ፍላጎት በትክክል አገናዝቦ ይበጃል ወይም የተሻለ ነው የሚል አንድ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የጌዲዮ ዞን ምሁራን ማህበር ከህዝብ ፍላጎት በመነሳት ከአባላቶቹ ጋር በጠቅላላ ጉባኤ ሊመክር መሆኑን አስታውቋል፡፡

በቅርቡ የሲዳማ ዞን በህዝበ ውሳኔ ወደ ክልልነት በማደጉ የጌድዮ ዞን ከደቡብ ክልል ጋር ያለው የየብስ ግንኙነት ይቋረጣል።

በዚህ ምክንያት የዞኑ ቀጣይ የአስተዳደር ሁኔታ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄዎች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡

የጌዲኦ ዞን ምሁራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ክብሩ ማሞ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በወቅታዊ የዞኑ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ምሁራኑ እንዲወያዩበት የሚፈለገው አጀንዳ የሚቀረፀው ከህዝቡ ሀሳብ በመነሳት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወራዳዎች የማህበሩ ተወካዮች ስላሉ እነርሱ ትክክለኛውን የህዝብ ፍላጎት አደራጅተው እንዲያቀርቡ መመሪያ ተሰጥቷቸው ስራ ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

እንደዚህ አይነቱ አካሄድ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ አይነተኛ ሚና አላቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ምሁራን ማህበር በሚያዘጋጀው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሀገር ውስጥም በውጪም የሚገኙ ከ500 በላይ አባላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ሰምተናል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው የሚከናወንበትን እለት የማህበሩ ቦርድ አባላት የፊታችን ቅዳሜ በሚያደርጉት ውይይት እንደሚወሰንም ሰብሳቢው የተናገሩ ሲሆን የዞኑ ቀጣይ የአስተዳደር ሁኔታ ቀዳሚ የህዝብ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው አቶ ክብሩ ለጉባኤው መሰረት የሚሆኑ ግብአቶች መጠናቀቃቸውን አሳውቀዋል፡፡

የጌዲዮ ምሁራን በጠቅላላ ጉባኤያቸው ከህዝቡ ፍላጎት በመነሳት የጌድዮ ዞን ከቀሪው በደቡብ ክልል ከሚገኙ 55ቱ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር አንድ ሆኖ ይቀጥል ወይም ለብቻው እንደ ክልል ይዋቀር በሚለው ሀሳብ ላይ ከስምምነት እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡