አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 1፣2012

የኖቤል ሽልማት አሸናፊው የኢትዮጵያ መሪ ዶ/ር አቢይ አህመድ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ በሽልማቱ ዙሪያ የነበረው ድባብ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል፡፡

ኦስሎ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በኢትዮጵያ ባነሮች ተውባ ሰነበተች፡፡

ሚዲያዎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ በኩራት መሰከሩ ያሉት ጠ/ሚሩ ኢትዮጵያን በድህነትና በጦርነት፣ በረሐብና በእልቂት የሚያውቋት ሁሉ አዲስ ታሪክ ሆነባቸው ሲሉ አስፍረዋል፡፡

በመላው ዓለም ተበትነው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብራቸውን ከፍ የሚያደርግ ሥራ በታሪክ ውስጥ ሲመዘገብ አዩ ሲሉ የገለጹት ዶ/ር አቢይ ልጆቻቸው በባዕድ ሀገር በታሪካቸው በዓረብ ሀገር የሚኖሩ ዜጎቻችን አሠሪዎቻቸው ወደታች ሳይሆን ወደላይ እንዲዩዋቸው የሚያደርግ ታሪክ በዓለም አደባባይ ሲከወን ዕንባ በተሞሉ ዓይኖቻቸው አደነቁ ብለዋል፡፡

በኦስሎ ያገኘነው ክብር የሀገራችን ጉዞ ከትናንት የዛሬው፣ ከዛሬውም የነገው እጅግ የተሻለ መሆኑን አመላክቶናል የሚሉት ተሸላሚው ጠ/ሚ ይህ ለኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይሆንም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እናዳለ ስለኢትዮ ኤርትራ የጦርነት አስከፊነት በሽልማቱ መድረክ ላይ ሲናገሩ “በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሞቱትን ጓዶቼን ዛሬም ድረስ አስታውሳቸዋለሁ፣ ስለ ቤተሰቦቻቸውም በጣም አስባለሁ” ያሉ ሲሆን ጦርነትን አይተው የማያውቁ ነገር ግን ጦርነትን የሚያሞግሱና ሮማንቲክ የሚያስመስሉ አሉ በማለት ይገልጻሉ።

በጦር ሜዳ ወንድም ወንድሙን ሲያርድ ወይም ሲገድል አይቻለሁ ሲሉ የተናገሩት ዶ/ር አቢይ አህመድ አዛውንት ወንዶች ፣ ሴቶች እና ልጆች ሞት በሚፈነጥቀው በጥይት እና በተኩስ ፍንዳታ ሲሸማቀቁ አይቻለሁም ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በተደረገው ጦርነት አንድ መቶ ሺህ ወታደሮች እና ሲቪሎች ህይወታቸውን አጥተዋል ያሉም ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቤተሰቦች እንዲፈርስ አድርጓል ሲሉ ገልጸው እንዲሁም በሁለቱም ወገኖች ማኅበረሰብ እስከመጨረሻው ጠባሳ ጥሎ አልፏል በማለት ያስረዳሉ።