አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 1፣2012

ከሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች ግድያ ጋር በተያያዘ በእነ ሻምበል መማር ጌትነት መዝገብ የተጠረጠሩ ግለሰቦች የክስ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 55 ግለሰቦች ላይ የክስ ማመልከቻ (ቻርጅ) ከተደመጠ በኋላ ነበር ለዛሬ የተቀጠረው።

በዛሬው ቀጠሮም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከሳሾችን የጽሑፍ የክስ መቃወሚያ ለመቀበል፤ ባለፈው ችሎት በህመም ምክንያት ያልቀረቡ አንድ ተከሳሽን የክስ ማመልከቻ ለማንበብ እና ባለፈው ችሎት ያልቀረቡ ሌሎች ተከሳሾችን ፖሊስ ስለማቅረቡ ለማረጋገጥ ነው የቀጠረው።

ባለፈው ቀጠሮ በህመም ምክንያት መቅረብ ያልቻሉትን 29ኛ ተከሳሽ ማንነትን ከተቀበለ በኋላ ፍርድ ቤቱ የክስ ማመልከቻውን አንብቦላቸዋል።

ያልተገኙ ተከሳሾችን በተመለከተ ፖሊስ አለማቅረቡን አስታውቆ ለሚቀጥለው ቀጠሮ እንደሚያቀርባቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው የክስ መቃወሚያቸውን ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አቅርበዋል።

ተደራራቢ ክሶች ሊደራረቡ እንደማይገባ፤ በቴክኒክ ማስረጃነት የቀረቡ የስልክ ልውውጦች ባለመቅረባቸው የድምጹን ማንነት ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑን፤ የንብረት ውድመትን በተመለከተ አለ የተባለው የሲዲ ማስረጃ አለመቅረቡን እና በአማራጭ የቀረበው ክስ ከተደነገገው ክስ እና ፍሬ ነገሩ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ተገቢነት የላቸውም የሚል መቃወሚያ ማቅረባቸውን የተጠርጣሪ ጠበቃ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የ3ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ፣ 13ኛ እና 52ኛ ተከሳሾች የባንክ ሒሳብ በምርመራ ወቅት የታገደ መሆኑን ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ገልጸው በዚህ ምክንያት ተጠርጣሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ በመውደቃቸው፤ የሒሳብ ቁጥሮቹ ከክሱ ጋር ተያያዥነት የሌላቸው እና በማስረጃነት ያልቀረቡ መሆናቸውን በመግለጽ እገዳው እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ጠበቆች አቤቱታቸውን እግዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በተጨማሪም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችን በሚቀጥለው ችሎት ያቅርብ ብሏል።

የዓቃቤ ህግን አስተያየት ለመቀበልም ለጥር 6/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።