አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 1፣2012

በወለጋ ዩኒቨርስቲ ትናንት ህዳር 30 ቀን 2012 አ.ም በሶስት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው በትላንትናው እለት ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ በወለጋ ዩኒቨርስቲ በሁለት ተማሪዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ዛሬ ማለዳ ላይም በአንድ ተማሪ ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው የማስተማሪያ አጠቃላይ ሆስፒታል ተገቢው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን ጉዳት አድራሽ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ቀናት በጎንደር ዩኒቨርስቲ ውስጥ አመጽ እና ብጥብጥ ለማስነሳት የሞከሩ እንዲሁም በአንድ ተማሪ ላይ ጉዳት በማድረስ ለህልፈት በመዳረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ የመመስረት ሂደት መጠናቀቁን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል ፡፡

በተያያዘ ዜና በደባርቅ ዩኒቨርሲቲም የመብራት ማቋረጥን ተገን በማድረግ ጥፋት ለማድረስ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ ተማሪዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘው በሴኔት ውሳኔ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን በተጨማሪም ክስ ተመስርቶባቸዋል ሲል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡

ከቀናት በፊት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከታህሳስ 6/2012 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በፌደራል ፖሊስ መጠበቅ እንደሚጀምሩና የዲጂታል መታወቂያም ተግባራዊ እንዲሆን እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በደህንነት ካሜራዎችም ለመከታተል የደህንነት ካሜራዎች በዩኒቨርሲቲዎቹ ለመትከል መመሪያ መስጠቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ ሀይለስላሴ የጸጥታ ችግር ስጋት እንደሌለባቸው ገልጸው ሆኖም በፌደራል ፖሊስ መጠበቅ በተማሪዎች ላይ የመደናገጥ እና የመረበሽ ስሜት እንዳይፈጠር ተማሪዎችን ማወያየት እና ስለሁኔታው ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው በፌደራል ፖሊስ መጠበቁ ከአካዳሚክ ነጻነታቸውን እንደማይጋፋ ገልጸዋል፡፡