አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 1፣2012

በጎንደር ከተማ አዘዞ ቀበሌ 19 ትናንት ምሽት አራት ሰዓት ተኩል አካባቢ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 3 የእህል ወፍጮ ቤቶችና አራት ጊዚያዊ የእህል መጋዘኖች ለጊዜው ግምታቸው ካልታወቁ ንብረቶች ጋር ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የከተማው ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር አበበ እንዳሉት ቃጠሎው የደረሰው በከተማው የአውቶብስ መናኸሪያ አጠገብ በሚገኙ ጊዜያዊ የገበያ ስፍራ አጠገብ ሲሆን በሰው ላይ ግን የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ገልጸዋል።

ለአንድ ሰዓት የዘለቀውን የእሳት ቃጠሎ  መቆጣጠር መቻሉን ጠቁመው እሳቱን ለማጥፋት በተደረገው ርብርብ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሁለት ሰዎች በጭሽ የመታፈን ጉዳት ደርሶባቸው የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

ፖሊስ ቃጠሎው ያደረሰውን የንብረት ውድመትና የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት የምርመራ ስራ መጀመሩንም ምክትል ኮማንደሩ አብራርተዋል፡፡