አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 2፣2012 ዓ.ም

“በሱዳን ብዙ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ህዝብ የስደት የኑሮ ጫና እንዳልበቃው ሰሞኑን ሃይለኛ አፈሳ እየተካሄደበት እንደሚገኝ የአሶሺየትድ ፕረስ ጋዜጠኛው ኤሊያስ መሰረት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

የአገሪቱ ህግ ማንኛውም የውጭ ዜጋ በመኖሪያ ፍቃድ እንዲኖር የሚያስገድድ ቢሆንም ይህ የመኖርያ ፍቃድ ለማውጣት 99% ያህሉ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ አይፈቅድለትም።

አብዛኛው የኢትዮጵያ ተወላጅ ዜጋ በነፍስ ወከፍ የሚከፈለው ደሞዝ የአገሪቱ ኑሮ ውድነት ያገናዘበ ባለመሆኑ በፊት በነበሩት አምባሳደር ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለኢትዮጵያውያን በተለየ ከኢሚግሬሽን መታወቂያ  በቅናሽ ክፍያ እንዲሰጥ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።

ይህ መታወቂያ በኢትዮጵያ አምባሳደር ለኢትዮጵያውያን የተጠየቀ ቢሆንም ኢሚግሬሽኑ ለሁሉም አፍሪካውያን መስጠት ጀምሯል፡፡

የዚህ መታወቂያ ዋጋ በወቅቱ በ100 ጂኔ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በአሁኑ ጊዜ 3,700 ጂኔ መድረሱ ተዘግቧል፡፡

ቢሮክራሲው ከሚባለው በላይ አስቸጋሪ በመሆኑና የመታወቂያ ፈላጊ ሰው በብዛት በመኖሩ መታወቂያውን ለማውጣት ከሚኖረው እንግልት በላይ መታወቂያው የዛሬ አመት እድሳት ማድረግ ሲጀመር ለስራ እንደማያገለግል ከበስተጀርባው እንደተጻፈበት ታውቋል።

በወቅቱ “ይህ እንዴት ይሆናል?” ተብሎ ሲጠየቅ “ለተቀጣሪ ሰራተኛ አይደለም፣ ትላልቅ ስራ ወይ ኢንቨስትመንት ለሚያደርጉ ታስቦ ነው የተፃፈው” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።

ይህ ሁሉ አልፎ ሰሞኑን “ይህንን መታወቂያ ይዛችሁ ስራ መስራት አትችሉም” በማለት በሰፊው አፈሳ እየተካሄደ ነው ተብሏል።

የሚገርመው እና አስደንጋጭ ያደረገው ደግሞ ስራ ሲሰራ የተገኘ ሰው ቅጣቱ በፍርድ ቤት 50,000 ጂኔ በመሆኑ ህዝቡ ከባድ ችግር ላይ ወድቋል።

ኤምባሲው ከሚመለከታቸው አከላት ጋር እየተነጋገርኩ ነው እንዲሁም  ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተነጋግሬለሁ ቢልም መንግስት አፈሳውን አላቆመም ሲል ዘገባው ያመለክታል።