አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 2፣2012 ዓ.ም

የኖቤል ሽልመቱ ዓለም ለምስራቅ አፍሪካ የሚሰጠውን እሳቤ የሚቀይር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

የዓለም የኖቤል የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የጀግና አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን ለክብራቸውም 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆን ሽልማታቸውን ከትናንት በስቲያ በኖርዌይ ርዕሰ መዲና ኦስሎ በተካሄደ ደማቅ ስነ ስርዓት መቀበላቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከተደረገላቸው አቀባበል በኋላ በሰጡት መግለጫም፣ “ለመላው የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።

በሽልማቱ ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን ስም ከፍ ያደረገ መሆኑን ገልፀው፤ ሽልማቱ ዓለም ለምስራቅ አፍሪካ የሚሰጠውን እሳቤ የሚቀይር” መሆኑንም አመላክተዋል።

ሽልማቱ እውን እንዲሆን በርካታ እናቶች አስተዋፆ እንዳበረከቱ እውቅና የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እውቅናው ለኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅ አገራትም ጭምር የተበረከተ ነውም ብለዋል።

በኖርዌይ ኦስሎ በተካሄደው ደማቅ የሽልማት ስነ ስርዓት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ በቀጥታ ስርጭት ሁነቱን መከታተሉን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁነቱ የአገሪቷን ገጽታ የቀየረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህን መልካም እድል በመጠቀምም በርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መሳብ እና ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠር ተግቶ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የድህነትና የጉስቁልና ታሪክ እንዲያባቃና የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን እንዲሁንም ሁሉም ተግቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ይህ ሽልማት በአዳዲስ ነገሮች እንዲደገም የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት  የጦርነት፣ የግጭት፣ የኋላ ቀርነት ታሪኮች እንዲያበቁና ቀጠናው እንዲበለጽግ  በጋራና በትብብር መስራት እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምስጋና የቸሩ ሲሆን፤ በቅርቡ እንደሚገናኙም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።