አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 2፣2012 ዓ.ም

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአስተዳደር ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችንና በጥቅሉ የዜጎችን የአስተዳደር እንግልት ይቀርፋል ያለዉን የአስተዳደር ስነ ስርአት ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የላከ ሲሆን አዋጁም በቅርቡ ሲፀድቅ እነዚህን ችግሮች ይፈታል ተብሎ እንደሚታመን ገልጿል፡፡

በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዝናቡ ቱኑ እንደተናገሩት የፌዴራል ተቋማት አገልግሎታቸዉን ለተገልጋዩ ህዝብ ሲሰጡ ግልፅነትን በመላበስ መሆን አለበት፡፡

በተጨማሪም ይህ አዋጅ ሲፀድቅ ተቋማቱ ማንኛዉም መመሪያ ካወጡ በኋላ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በመላክ አስተያየቶችና ግብአቶች የሚሰጥበት መሆኑን ጠቁመዉ ይህ አሰራርም ተጠያቂነትን አብሮ የያዘ በመሆኑ ካሁን በፊት ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ የራሱ ሚና እንደሚኖረዉ ገልጸዋል፡፡

እስከአሁን ባለዉ አሠራር የአስተዳደር ተቋሞች ስለ ህግ አወጣጣቸውና ውሳኔ አሰጣጣቸው አስመልክቶ እንዲሁም በእነዚህ ተግባሮቻቸው ቅር የተሰኙ ወገኖች ስለሚኖራቸው መፍትሄ የተቀመጠ ሥርዓት ባለመኖሩ የዘፈቀደ አሠራር ስፍኖ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር እጦት ምንጭ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ሆኖ መቆየቱን ያወሱት ዳይሬክተሩ ይህ አዋጅ መዘጋጀቱ በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት በመድፈን የጎላ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአስተዳደር ሥነሥርዓት ሕግ ሊያሳካቸው የሚገቡ ሕገመንግስታዊ ዓላማዎችን በመግለፅ የዜጎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስተዳደር ተቋማት ያለአግባብ እንዳይሽራረፉ፣ የአስተዳደር ተቋማት የውክልና ሥልጣን በሕግ እና በሥነሥርዓት ማዕቀፍ መመራት እንደሚያስፈልገው፤ በመታመኑና መንግስታዊ አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና፤ ማናቸውም የመንግስት ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን የተመላከተ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰዉ የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ሥርዓት የሚደነግግ በመሆኑ አስተዳደራዊ ፍትህን በማስፈን በኩልም አዋጁ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡