አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 2፣2012 ዓ.ም

የሰላም ኖቤል ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሰጠቱ ትክክለኛና የሚገባቸው መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ አስታወቁ።

የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የሰላም ኖቤል ሽልማት ላገኙት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ የደስታ መግለጫ ስነ ስርዓት አካሄደዋል።

በዚህ ስነስርዓት ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሸነፉበትን የሰላም ኖቤል ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ክብር አብራርተዋል።

“ በሰላም እና መረጋጋት ያገኘውን አንፀባራቂ ድል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም በጋራ መስራት ይገባናል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የዶክተር አብይ የኖቤል ሰላም ሽልማት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም እንዲቆም ያነሳሳ ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የተናገሩት በክልሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትን አስመልክቶ በተዘጋጀው የእንኳን ደስ አለን ፕሮግራም ላይ በመገኘት ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት አገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበትና ፋታ በማይሰጡ ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች በተከሰቱበት ባለፉት 18 ወራት የስልጣን ቆይታ ነው።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ እያንዳንዱ ዜጋ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ተገንዝበን ሁላችንም የድርሻችንን ማበርከት ይጠበቅብናል።

ይህ በአንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የዓለም የኖቤል ሽልማትን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይም ‹‹ሽልማቱ ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ከፍ ያለ ዝናና ክብር እንድትጎናጸፍ አድርጓል›› ተብሏል፡፡ ‹‹ታላላቅ መሪዎች የሚፈልቁባት፣ ለሠላም ለአንድነት እና ለፍቅር የሚታገሉ ምሁራን የተፈጠሩባት ኢትዮጵያ በልጽጋ አንድነቷን አስከብራ ትኖራለች›› የሚሉ ሐሳቦች በውይይቱ መነሳቱም ታውቋል፡፡