አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 5፣2012

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) በማንኛውም መልኩ መከልከሉን ደንግጎ እያለ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ድንጋጌውን በመጣስ፣ በደንበኞቻቸውና በእነሱ መካከል ብቻ ሚስጥር ሆኖ መጠበቅ ያለበት የሰነድ ማስረጃ ላይ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑን ጠበቆች ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

የማረሚያ ቤቶቹ ድርጊት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የጣሰ በመሆኑ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አቤቱታ ያቀረቡት፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማና በአዲስ አበባ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው 13 ተከሳሾች ጠበቆች ናቸው፡፡

ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በደንበኞቻቸውና በእነሱ መካከል መጠበቅ ያለበትን ሚስጥር እያዩና ሳንሱር እያደረጉ ነው በማለት ይኼ ደግሞ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ በመሆኑ፣ ሊከለከል ስለሚገባ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሾቹ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ችሎት ካቀረቡ በኋላ፣ አቤቱታ እንዳላቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው አቤቱታውን አሰምተዋል፡፡

ፖሊስ ያለ ምንም ምክንያት ንብረታቸውን መያዙንና ለፍርድ ቤትም ቢያመለክቱም መፍትሔ እንዳላገኙ፣ በጊዜ ቀጠሮ ላይ እያሉ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም እንዲመለስ ትዕዛዝ የሰጡ ቢሆንም፣ ትዕዛዙ ተግባራዊ ሊደረግላቸው እንዳልቻለ በአቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ንብረቶቻቸው በምርመራ መዝገብ ላይ የተመዘገቡ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹን ንብረቶች ግን ፖሊስ ያለ ደረሰኝ የወሰዳቸው በመሆኑ ‹‹ቢጠፉ ተጠያቂ የምናደርገው ማንን ነው?›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡

በብርበራ ወቅት የሚወሰዱ ንብረቶች ተቆጥረውና ዓይነታቸው ጭምር ተገልጾ መረከቢያ ሰነድ ለተጠርጣሪ መስጠት ቢኖርበትም፣ ባለመደረጉ ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡