አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 6፣2012

በኦሮሞና በአማራ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሁለቱ ህዝቦችን ሁለንተናዊ ትስስር በማጉላት የሚስተዋሉ የፖለቲካ ተቃርኖዎችን ሊፈቱ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በአሮሚያና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ሊሂቃን የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በርካታ የጋራ የሆኑ እሴቶች ያላቸውን ህዝቦች ናቸው ያሉት የታሪክ ምሁሩ አቶ ሲሳይ አውግቸው ሁሉቱ ህዝቦችም ዘመናዊ ኢትዮጵያን በመገንባት ረገድ በጋራ መታገላቸውንም አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ባሉ የታሪክ ምልከታዎች ምክንያት የሁለቱ ህዝቦችን የሚያራርቁ ትርክቶች መኖራቸውንም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ህዝቦችን ሁለንተናዊ ትስስር በማጎላትም የሚስተዋሉ የፖለቲካ ተቃርኖዎችን ሊፈቱ እንደሚገባም አቶ ሲሳይ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ ወደ ስልጣን ለመምጣት ጦርነትና አምጽ አማራጭ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት ፖለቲከኛው ዶክተር ዲማ ነገዎ ይሄንንም ለመቅርፍም ፖለቲካውን በንግግር የሚያምን ስልጡን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የውይይት መድረኩ ፖለቲከኞች ከጥርጣሬ መንፈስ ወጥተው በቅንጅት እና በመግባባት መስራት እንዲችሉ በር የሚከፍት መሆኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ውይይቱ ለ2 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተለያዩ የጋራ ጉዳዩ ላይ መግባባት በመድረስ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሁለቱ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ቀደም ሲል የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና የአገሪቷን ሠላም ለመመለሰ በጋራ እንደሚሰሩ ከስምምነት ደርሰዋል።

በዚሁ መሰረት ከሰሞኑ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰቱ ችግሮችን ተከትሎ መፍትሄ ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነው ዛሬ እየመከሩ ያሉት።

ከዚህ ቀደም በሁለቱ ክልሎች ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነትን ማጠናከርና ሠላም ማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ሲወያዩ ቆይተዋል።

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ሰባት ፓርቲዎች በክልሎቹ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።