አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 7፣2012

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርስቲዎች በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑ የሚታወስ ነው ይህንንም ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የፀጥታ ሃይሎችን በልዩ ሁኔታ መመደቡን አስታውቋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አዳዲስ ተመራቂ የፖሊስ አባላትን ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በቋሚነት የመመደቡ ስራ እየተከናወነ ሲሆን የጸጥታ ሃይሎች በሌሎች ክልሎች ባሉ ዩኒቨርስቲዎችም ይመደባሉ ሲሉ የኮሚሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ ተናግረዋል፡፡

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ዩኒቨርቲዎች ጥበቃዎችን ለማጠናከር ያስፈለገው  ግጭቶች ጎልተው የሚታዩባቸው በመሆናቸው መሆኑንም እንደምክንያትነት አንስተውታል፡፡

ኮሚሽኑ አዳዲስ ተመራቂ የፖሊስ አባላትን ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በቋሚነት የመመደቡ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፤ ጥበቃው ከመጣ በኋላ መረጋጋት የሚታይ ቢሆንም አሁንም ግን ተማሪዎች ላይ ስጋቶች መኖራቸውን ነው አቶ ጄይላን የገለጹት በመሆኑም ይህንን የተማሪዎች ስጋት በማየት ጥበቃውን በማጠናከር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አዳዲስ ምሩቅ ፖሊሶች ሀገሪቷ ካለችበት ቀውስ ጋር ተያይዞ፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ሁሉንም ህብረተሰብ በቅንነት ያለ አድሎ እንዴት ማገልገል አለባቸው በሚለው ላይ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተማራቂዎቹም መካከል የተወሰኑት በቋሚነት ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገቡ እና ፀጥታ የማስከበር ስራቸውን እንደሚጀምሩ አቶ ጀይላን የገለጹ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ተፈጥረው በነበሩ ችግሮች ምክንያት ከዚህ ቀደም የነበሩ ፌደራል ፖሊሶች፣ መከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች አዲስ ከሚመደቡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ጋር ተቀናጅተው የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላም ለመጠበቅ ይሰራሉም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚመደቡት የፀጥታ ሀይሎች ቁጥር አለመታወቁን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣እንደ ዩኒቨርሲተዎቹ ፍላጎት እና የፀጥታ ሁኔታ ቁጥራቸው እንደሚለያይ ተናግረዋል፡፡