አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 7፣2012

በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ የውጪ ባለሀብቶች ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የመኖሪያ ቤት እንዲገነቡ በረቂቅ ህጉ አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ ተደንግጓል፡፡

ረቂቁ ዛሬ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ሲደረግበትም ከእንደራሴዎቹ መካከል፣ ለመኖሪያ የሚሆን መሬት የማግኘት እና መኖሪያ ሕንፃ መገንባት የመሳሰሉ ቋሚ ንብረቶችን ማፍራት ለኢትዮጵያዊያን ዜጎች ብቻ የተሰጠ እንደሆነ በህገ መንግስቱ ተደንግጓል ብለዋል፡፡

በረቂቅ ህጉ የውጪ ኢንቨስተሮች የተጠቀሰውን ቋሚ ሀብት እንዲያፈሩ በረቂቁ መደንገጉ ህገ መንግስቱን ይቃረናል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡

ድንጋጌው ህጉ ከመውጣቱ በፊት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የቆዩ የውጪ ዜጎችን ቤት መገንባት እንዲችሉ የሚፈቅድላቸው ነው፡፡

በመሆኑም ህጉ ከመፅደቁ በፊት የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን እንዲያጤነው እንደራሴዎቹ ጠይቀዋል፡፡