አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 09፣2012

በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የእርስ በርስ ግጭትና አላስፈላጊ የጸጥታ ችግሮች የተከሰቱ በመሆኑ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰ እንደሚገኝ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕረስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የሁለቱ ክልሎች የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ምሁራን ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን የፖለቲካ ድርጅቶች፣የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎችን የክልሎችን የቆየ መልካም ትስስር ለማጠልሸት የሚሞክሩ ሀይሎችን ሴራ ለማክሸፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በሁለቱ ክልሎች የሚንቀሳቀሱና ስምንት የሚደርሱ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን በመጥራት በዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ አወያይተው የፖለቲካ አባላትን ለማንቀሳቀስ፣ለመመረጥ፣ የፖለቲካ አጀንዳን በተገቢው መንገድ ለህዝብ ለማድረስ እና ህዝብ ለመምራት በመጀመሪያ ማረፊያ የሚሆን ሰላሙ የተረጋገጠ ህዝብ ሊኖር እንደሚገባ ከስምምነት ደርሰዋል ያሉት አቶ ንጉሱ የምንመራው ህዝብ በግጭት እና ባልተገባ እንቅስቃሴ ለሞት እየተዳረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመሆናቸው የሀገር ሽማግሌዎች፣ምሁራን፣ባለሀብቶች፣የሀይማኖት አባቶች፣አክቲቪስቶችና የፖለቲካ መሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ በመምከር ከስምምነት መድረስ ከቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ሰላማዊ ማድረግ ይቻላል ፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት በተደረገው ውይይት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችም ጭምር መልካም አርዓያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለፉ እኩይና ሰናይ ክስተቶችን በመመዘን ከአሁን በኋላ ብዙ ስህተቶች እንዳይደገሙ ያግዛል ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር የፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶችን ለማቀራረብ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡