አባይ ሚዲያ ዜና- ታህሳስ 09፣2012

ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውና ሀገሪቱን ለከፍተኛ ስጋት ጥሏት የከረመውን አንበጣ ለመከላከል ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ስምምነት ብታደርግም ሀገራቱ ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀዉ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባዉን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከጎረቤት አገራት ስምምነት ላይ ቢደረስም ስምምነቱን ግን እየተገበሩ አይደሉም ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከሱማሊላንድ አመራሮች ጋር አንበጣን ለመከላከል ስምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግን የመከላከል ስራዉን እየደገፉ አለመሆናቸዉ ታዉቋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ እንዳስታወቁት የመንና እና ሶማሊላንድ አንበጣዉን ባለመከላከላቸዉ በየቀኑ ወደ አገር የሚገባዉ አንበጣ አለመቆሙን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በሶማሌ ክልል አይሻ ደዋሌ እና ቀብሪዳሃር ተብለዉ በሚጠሩት አካባቢዎች ከፍተኛ የአንበጣ ስርጭት እንዳለም ታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከባለፈዉ አመት ሰኔ ወር ጀምሮ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን የመከላከል ስራዉን እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፤ጎረቤት አገሮች ድጋፍ ባለማድረጋቸዉ በስራዉ ላይ ጫና አሳድሮብናል ብለዋል፡፡

የሱማሊላንድ መንግስት የአንበጣ መንጋዉን ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመከላከል የተስማማ ቢሆንም አካባቢዉ በራሃማ በመሆኑ አስተዳደሩ ለማገዝ ፍቃደኛ አይደለም ነዉ የተባለዉ፡፡

ይህም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስራ ጫና እንደፈጠረና ተምችን የመሳሰሉ ተባዮችን ለመከላከል እንዳልቻለም አስታዉቋል፡፡

ይሁን እንጂ አዲስ መጤ ተምች እና ሌሎች ተባዮችን አርሶ አደሩ እየተከላከለ እንደሆነም አቶ ዘብድዮስ ተናግረዋል፡፡

በየቀኑ ወደ አገር የሚገባዉን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በ4 አዉሮፕላኖች እየተሰራ ያለዉ የመድሃኒት ርጭት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ሰምተናል፡፡