አባይ ሚዲያ ዜና – ታህሳስ 11፣ 2012

በምስራቅ ጎጃም ዞን ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ሞጣ ከተማ አስተዳደር ዛሬ አመሻሽ ላይ ጀምሮ በከተማዋ በሚገኘው የታላቁ ጀሚዑል ኸይራት መስጂድና ሌሎች ሁለት መስጅዶች መቃጠላቸውን የአባይ ሚዲያ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ትላንት ታህሳስ 10/2012 አመሻሹ ላይ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ ባልታወቀ ምክንያት እሳት መከሰቱን ተከትሎ ሰው በሐይማኖቱ ሳይለያይ ተረባርቦ ለማጥፋት ጥረት አደረገ ተሳካና ሰው ወደ መጣበት መመለስ ጀመረ በማለት ያስረዳሉ፡፡

ከመቅጽበት ሁነቱን የማይገልጽ አሉባልታ መሰራጨት ጀመረ ከተለያዬ ቦታ ተደፈርን የሚሉ ሰዎች መሳሪያቸውን እየተኮሱ መጡ የሚሉት ነዋሪው ወዲያው ከተማው መሐል የሚገኘውን ትልቁን መስጅደል ኸይራት አቃጠሉ። ይህም አልበቃ ብሎ በሆታና በጭፈራ ሁለት ተጨማሪ መስጂዶችን አቃጠሉ ሰሉ ነግረውናል፡፡

አንደኛው ላይ ደግሞ ድንጋይ በመወርወር መጠነኛ ጉዳት አደረሱ  በአጠቃላይ ሦስት መስጅዶች ሲቃጠሉ አንደኛው በድንጋይ ድብደባ ደርሶበታል ብለዋል፡፡

ይህም ያልበቃቸው እነዚህ ማንንም የማይወክሉ አውዳሚዎች በርካታ የከተማው ሱቆችን አቃጠሉ፣ ዘረፉም በማለት የሚገልጹት ነዋሪው ከምሽቱ 3 ስዓት ላይ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ መረጃው እንደደረሳቸው ልዩ ሀይላቸውን ልከው ሙሉ በሙሉ ማረጋጋት ችለው ነበር ነገር ግን አጥፊዎችን የመያዙ ሂደት ገና ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ነዋሪው እንደሚሉት እነዚህ ከየቦታው ተጠራርተው የመጡ አሸባሪዎች ከተማውን ሞልተው ለጥቃት ሲዘጋጁ የከተማው ፖሊስ እጁን አጣጥፎ ይመለከት ነበር ሲሉ ገልጸው ፖሊስ ትብብር ቢያደርግ ኖሮ ብዙ ውድመት ሳይከሰት መቆጣጠር ይቻል ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የጸጥታ ችግሩ ሙሉ የተረጋጋ ሲሆን በውድመቱ ዙሪያ መግለጫ የሰጠው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሞጣ ከተማ በተፈጸመው ድርጊት ማዘኑንና ድርጊቱን እንደሚያወግዝ  አስታወቋ፡፡

የምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሰኢድ አሕመድ ትላናት ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አጸያፊ ተግባር መፈጸሙን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

በሞጣ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ አራት መስጂዶች መቃጠላቸዉንና የሙስሊም ሱቆችና ድርጅቶች ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን ገልጸዋል።

‹‹በተፈጸመው ድርጊት የተሰማንን ሐዘን እንገልጻለን፤ አስጸያፊ ድርጊቱንም እናወግዛለን›› ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።

መንግሥት ድርጊቱን በፈጸሙ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም ሼህ ሰኢድ አሕመድ ጠይቀው መንግሥት ለሁሉም ቤተ እምነቶች ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግም አሳስበዋል።