አባይ ሚዲያ ዜና – ታህሳስ 12፣2012

የዕርቀ -ሠላም ኮሚሽን አባላት በቀጣይ አብሮ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዩች ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ጋር በአሶሳ ውይይት አድርገዋል፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጠረው የነበሩ ግጭቶች፣መፈናቀል እጅግ አስከፊ የነበሩ እና የዜጎችን የመኖር መብት የተፈታተኑ እንደነበሩ ያስታወሱት በውይይቱ ላይ የተገኙት የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በመላ ሀገሪቱ ህዝቦች ተባብረውና ተጋግዘው እንዲኖሩ ለማድረግ የዕርቀ-ሠላም ኮሚሽን ይሰራል» ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አክለውም በዜጎች መካከል መጠራጠር እንዳይኖር፣ በደል እንዳይደርስ እንዲሁም የተፈጸሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ደግሞ በማጣራትና ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ተባብረው በሁሉም ቦታዎች ተዘዋውረው እንዲሰሩና እንዲኖሩ ማድረግ አንዱ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ተግባር ነው፡፡

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት የተሠጠውን ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ ግጭት የተስተዋሉባቸው አካባቢዎችን ጨምሮ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ዕርቅ እንዲወርድ፣የተበደለ እንዲካስና ፍትሕ እንዲሰፍንም ይሰራል ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሐሰን በበኩላቸው በክልሉ በህዝቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት አለመኖሩን የገለጹ ሲሆን በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች የሚስዋሉ ግጭቶች በተፈጥሮ ሀብት ይገባኛል እና በግለሰብ ደረጃ ያሉ ናቸው ይላሉ፡፡

የዕርቀ ሰላም ኮሚሽኑ የሚደርጋቸውን ተግባራት በጥንቃቄና በጥናት ላይ በመመስረት መሆን እዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በዚው አካባቢ ኢ- መደበኛ የተባሉ አደረጃጀቶች እና ከአጎራባች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የታጠቁ ሀይሎች መኖርና ለህግ ተገዥ ያለ መሆን ለዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ስራ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ስጋት የገለጹት ደግሞ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ ናቸው፡፡

በተለይም አልፎ አልፎ በታጣቂዎች የሚደርሱ ጥቃቶች እና የመንገድ መዘጋት የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚገድቡ ናቸው ብለዋል፡፡