አባይ ሚዲያ ዜና – ታህሳስ 12፣2012

ባሳለፍነው ሳምንት የወጣ አንድ ዘገባ ኢትዮጵያ መሰረቱን በጅቡቲ ጠረፍ አካባቢ፤  ዋና ማዘዣዉን ደግሞ ባህር ዳር ያደረገና በደቡባዊ የቀይ ባህር መግቢያ አካባቢ ጠንካራ የባህር ሀይል ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይህም ከህዳሴዉ ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽን በጥርጣሬ ማየቷ ከፍ ያለዉ ኢትዮጵያ ትልቅ ጫና መፍጠሪያ መሳሪያ እንደሚሆናት የግብጹ አል-ሞኒተር ጋዜጣ በሰፊው የአፍሪካ ፖለቲካ ትንታኔ አምዱ ይዞ ወጥቷል።

እንደ ዘገባው ከሆነ ታህሳስ 4 የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ለጅቡቲው አቻቸዉ ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ስልክ መተዉ፣በቀጠናዉ ብሎም በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸዉን አስረግጠዉ ነገሯቸዉ፡፡

ግብጽ ቀጥሎም በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ሶማሊያዊያን ሰብአዊ ድጋፍ የሚዉል ቁሳቁስ በጦር አዉሮፕላን ጭና ወደ ሶማሊያ ላከች፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድም ቢሆን አርፈዉ አልተቀመጡም፤ ከኢስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በሚገባ ምክክር ከማድረግ ባሻገር ፈረንሳይ ለባህር ሃይል ግንባታዉ ድጋፍ ማድረግ የሰዉ ሃይል ማሰልጠን በምትችልበት ሁኔታ ላይ ሳይቀር መክረዉ አወንታዊ ምላሽን አግኝተዋል፡፡

አል-ሞኒተር ከግብጽ ታማኝ ምንጮች አገኘሁት ባለዉ መረጃ መሰረት፣ይህ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በግብጽ ላይ ከፍተኛ ስጋትና ጭንቀትን መፍጠሩን ይገልጻል፡፡

ስጋቱ የተፈጠረዉም የህዳሴዉ ግድብ ዉይይት መቋጫ ዉል ሳይታወቅ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል መመስረት የሚፈጥረዉ ጫና ይኖራል በሚል መሆኑን ዘገባዉ ይጠቁማል፡፡

ቀይ ባህር አለማቀፋዊ ንግድ የሚጧጧፍበት መስመር ሲሆን በቀን ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ ይንቀሳቀስበታል።

ግብጽ፣ሱዳን፣የመን፣ሳዉዲ አረቢያ፣ጆርዳንና እስራኤል ዋና መናሃሪያቸዉ ነዉ፡፡

ግብጽም በዚህ በሜድትራኒያን ባህር ላይም ጠንካራ የሚባሉ የባህር ሃይሎች አሏት፡፡

ኢትዮጵያ አቋቁመዋለሁ ያለችዉ የባህር ሃይል፣ ግብጽ በህዳሴዉ ግድብ የምትዝተዉን ያህል ለራሷ ግድቦችም አስጊ ሆኖ የአቅም ተገዳዳሪነት የሚፈጥር እንደሚሆንም ታስባለች፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ የሚታወቁት አህመድ አስካር የተባሉ ምሁር፣ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ጠንካራ የባህር ሃይል በማቋቋም በቀጠናዉ ያላትን ሃያልነት ማስጠበቅ ትፈልጋለች።

ይህ እንዲሆን ደግሞ ግብጽ አትፈቅድም ሲሉ ጽፈዋል፡፡ይህ ቀጠና ለሁለቱ ሀገራት ተጨማሪ የዉዝግብ መነሻ ሊሆን እንደሚችልም ዘገባዉ ያትታል፡፡

ግሎባል ፋየር ፖዌር የተባለ ተቋም ባወጣዉ የ2019 የሀገራት ሁለንተናዊ ወታደራዊ አቅም ኢትዮጵያ ከ137 ሀገራት 47 ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ግብጽን ደግሞ 12ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል ሲል የዘገበው ኢትዮ ኤፍ ኤም ነው፡፡